በአማራ ክልል ወረዳዎች መጋዝን ውስጥ የተቀመጠ የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ በፍትሀዊነት እንዲሠራጭ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

86

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለውን የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ሂደት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙባረክ ኤልያስ፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ አጀበ ስንሻው፣ በግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦትና ገጠር ፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግስቱ ተስፋ ጨምሮ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ/ም በምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብና ሰሜን ሜጫ ወረዳዎች ተገኝተው የሁለት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሥራ እንቅስቃሴ ምልከታ አድርገዋል።

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በደጎይ ኅብረት ሥራ ማኅበር 1365 ኩንታል ዳፕ ማዳበሪያ እንዲሁም በወተት ዓባይ ኅብረት ሥራ ማኅበር 2 ሺ 800 ኩንታል ዳፕ ማዳበሪያ በመጋዝን ተከማችቶ አግኝተዋል። የወረዳ አመራሮች ለምን ለአርሶአደሮች እስካሁን እንዳላሰራጩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የቀረበው ማዳበሪያ አነስተኛ በመሆኑ ለሁሉም አርሶ አደር ማዳረስ ስለማንችል ተጨማሪ ማዳበሪያ እስኪመጣ እየጠበቅን ነው ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከመስክ ምልከታ መልስ በኋላ ከአርሶ አደሮች ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ለበቆሎ ዘር የሚሆን የማዳበሪያ እጥረት አጋጥሞናል፣ የቀረበውም ቢሆን ስርጭቱ ፍትሀዊ አይደለም፣ ማዳበሪያ በህገ ወጥ መንገድ እየተሸጠ ነው የሚሉና መሰል አስተያየቶች አርሶ አደሮች አቅርበዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ሀገራዊ ችግር መሆኑን ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙባረክ ኤልያስ፤ መንግስት የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናገረዋል። በመስክ ምልከታው ከአርሶ አደሩ ጠቃሚ ግብዓት እንደተገኘ ጠቅሰዋል። የማዳበሪያ ስርጭቱ ፍትሀዊ መሆን እንዳለበት ገልፀው አንድም ማዳበሪያ መጋዝን ውስጥ ሊኖር አይገባም ብለዋል። የግብርና ባለሙያዎች በኅብረት ሥራ ማኅበራት ተገኝተው የማዳበሪያ ስርጭቱን መከታተልና መቆጣጠር እንዳለባቸው አቶ ሙባረክ ኤልያስ ጠቁመዋል። የአቅርቦት እጥረቱን ተከትሎ የሚታየው ህገ ወጥ የማዳበሪያ ንግድ አርሶ አደሩ ታግሎ ማስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል።

ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት መጋዝን የገባው የአፈር ማዳበሪያ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አርሶ አደሮች ማሰራጨት እንደሚገባ የተናገሩት በግብርና ሚኒስቴር የግብዓት አቅርቦትና ገጠር ፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግሥቱ ተስፋ፤ የአፈር ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ እየተራገፈ መሆኑን ገልፀዋል። በቆሎ ከሚዘሩ ውስጥ ደጋማ አካባቢዎች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው፤ በዚህ ሳምንት 350 ሽህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እንደሚገባ ገልፀዋል። አርሶ አደሩ ተረጋገቶ ሳይረበሽ በትእግስት እንዲጠባበቅ ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን የቢሮው ሕዝብ ግንኙነት መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲስ አበባ የኪነ ጥበብ አቅሟን ማሳደግና ለጎብኝዎች መዳረሻነት መብቃት እንድትችል መሥራት ይገባል” አቶ ሰርጸ ፍሬ ስብሃት
Next articleበደብረ ታቦር ከተማ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ተመረቁ።