
ባሕር ዳር : ግንቦት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ነባር ሥርዓት ከስሞ አዲስ ሥርዓት የሚፈጠርበት ክስተት ተፈጥሯዊ እስኪመስል ድረስ ተደጋግሞ ተስተውሏል፡፡ በእነዚህ የሀገረ-መንግሥት ለውጦች መካከል የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ስብራቶች የሚፈጥሯቸው በርካታ ሀገራዊ መቋሳቆሎች ተከስተውም አልፈዋል፡፡ ምንም እንኳን በአብሮነት መካከል ግጭት ተፈጥሯዊ ቢኾንም የፖለቲካ አተካራዎች የሚፈጥሯቸው አለመግባባቶች ግን ውለው ሲያድሩ ሀገራዊ ቅራኔ ኾነው ብቅ ሲሉም ተስተውሏል፡፡
በበርካታ ሀገራት መካከል የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ስብራቶች ወደ ቅራኔ አድገው ጦር ሲያማዝዙ እና ላልተፈለገ መስዋዕትነት ሲዳርጉ ታይቷል፡፡ ሁሉም የዓለም ሀገራት እና አህጉራት መሰል ችግሮች አጋጥሟቸዋል እስኪባል ድረስ በአራቱም አቅጣጫ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች፣ የርስ በእርስ ግጭቶች እና መሰል ምስቅልቅሎች ታይተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሀገራት ችግሮቹን የፈቱበት እና የተሻገሩበት መንገድ ሀገርን ከጥፋት፤ ሕዝብን ከጉዳት የታደጉ ሲኾኑ የተወሰኑት ደግሞ አብሮ መኖር እስኪሳናቸው ድረስ ድንበር ተሸናሽነው ዳግም ላይገናኙ ተለያይተዋል፡፡ ይህ ከዓለም ሀገራት ታሪክ ኢትዮጵያዊያን ሊማሩት የሚገባ ሀቅ ነው የሚሉ አሉ፡፡
ኢትዮጵያ ቀደምት ሀገረ-መንግሥት ካጸኑ እና ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ካነበሩ ጥቂት ግንባር ቀደም ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ ዘመናዊው የመንግሥት አሥተዳደር ሳይታወቅ እና ሳይተዋወቅ ኢትዮጵያዊያን በሕግ ልዕልና የሚያምኑ፤ ለፍትሕ የሚታመኑ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ እንግዳን ተቀብሎ ማልመድ ነባር እሴታቸው እንደኾነ የሚነገርላቸው ኢትዮጵያዊያን ልዩ የሚያደርጋቸው በልዩነት ውስጥ ሀገራዊ አንድነትን ማጽናት መቻላቸው ነበርም ይባላል፡፡ “አንድ መኾን አንድ ዓይነት መኾን ማለት አይደለም” የሚለውን ሃሳብ በተግባር ኖረውታል ተብሎም ይታመናል፡፡
በዘመናት መካከል የጸናችው ኢትዮጵያ በየዘመኑ ብቅ ብለው ያለፉ በርካታ መንግሥታዊ ሥርዓቶችን አስተናግዳለች ያሉን የሕግ አማካሪው አደራው አዲሱ ናቸው፡፡ በእነዚህ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ታሪክ ለዘመናት የሚያስታውሳቸው መልካም ሥራዎች የመኖራቸውን ያክል ቅራኔ እና ቁርሾ የፈጠሩ አለመግባባቶችም ታይተዋል ይላሉ፡፡ ታሪክን እንደ ታሪክ ወስዶ ከታሪክ መማር አስፈላጊ ቢኾንም በታሪክ መቆራቆስ እና መነታረክ ግን በተለይም በዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር ሚዛን ሲደፋ ይስተዋላል ነው ያሉት አቶ አደራው፡፡
በሽግግር ወቅት የተፈጠሩ እና በሕዝብ መካከል የተስተዋሉ ግጭቶችን እያስታመሙ የተረጋጋ ሀገረ-መንግሥት መገንባት ህልም ነው የሚሉት የሕግ አማካሪው ፍትሕን ማስፈን እና ይቅርታ ማድረግ የሰከነ ሀገር ለማየት የግድ ይላል ይላሉ፡፡ እንደ ሕግ አማካሪው እነዚህን የቆዩ ቅራኔዎች ለመፍታት በዳይ ክሶ እና ተበዳይ ተክሶ የሚጸና ፍትሕ ያስፈልጋል፡፡ በሀገረ-መንግሥት ለውጦች እና በፖለቲካ ስብራቶች የተፈጠሩ ቅራኔዎችን በዘላቂነት ለማከም የሽግግር ፍትሕ በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ለውጥ ያመጣ አሠራር ነው፡፡
የሽግግር ፍትሕ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ሊታዩ የማይችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ የሥነ-ልቦና ስብራቶችን እና ውድመቶችን በተለየ የፍትሕ ሥርዓት መመልከት ነው የሚሉት አቶ አደራው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር ሙከራ አድርጋ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ለምሳሌ ያክል በሽግግር መንግሥት ወቅት የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር ሙከራ ተደርጎ ነበር ያሉት አማካሪው በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ሂደቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ጠምዝዞታል ይላሉ፡፡
በአሁናዊቷ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በቅርቡ ወደ ትግበራ ተገብቷል የሚሉት አቶ አደራው ሀገራዊ ምክክር ለምታልም ሀገር የሽግግር ፍትሕ ቀዳሚውና ትኩረት የሚያሻው አጀንዳ ነውም ይላሉ፡፡ ይቅርታ የሚወርደው እና ምክክር የሚጸናው ፍትሕ ርትእ ስታገኝ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ለዘመናት በነበረ ፖለቲካዊ መቋሰል የተፈጠረ ቅራኔ በፍትሕ ሊቃኝ ግድ ነው ይላሉ፡፡ የሽግግር ፍትህ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ሊታዩ የማይችሉ ጉዳዮችን የሚያይ እና ለአጭር ጊዜ የሚቆይ በመኾኑ በትግበራ ወቅት ልዩ ክትትል እና ድጋፍም ያስፈልገዋል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ሕዝብ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት በተረቀቀው እና 1987 ዓ.ም በጸደቀው ሕገ-መንግሥት ውስጥ በቂ ውክልና እንዳልነበረው ተደጋግሞ ይነሳል ያሉት የሕግ አማካሪው ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ለተፈጠሩና ማንነትን መሰረት ላደረጉ ጥቃቶች ሕገ መንግሥታዊ ከለላ ያላቸው እስኪመስሉ ድረስ እውቅና ተነፍጓቸዋል ነው የሚሉት፡፡ ከእንደዚህ አይነት የአፈጻጸም ክፍተቶች ለመዳን እና በሽግግር ፍትሕ የደረሱ ሰብዓዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃቶችን በሽግግር ፍትሕ ለማሳየት በቂ የልሂቃን ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በምክንያት መሞገት፣ በዕውቀት መከራከር እና በማስረጃ ማረጋገጥን በሚጠይቀው የፍትሕ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መኾን ግድ ነው የሚሉት አማካሪው ከጅምላ ጩኸት እና ካልተጠና ሂደት በመራቅ በሰከነ እና ለውጥ ማምጣት በሚችል መንገድ ጉዳዩን ማየት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ ውክልና ኖረውም አልኖረውም ላለፉት ጊዜያት ሲመራበት ቆይቷል የሚሉት አቶ አደራው አኹን ላይ ተመሳሳይ ክፍተቶች እንዳይኖሩ “ከሕገ-መንግሥቱ የዝግጅት ወቅት መማር ይገባል” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!