2015 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዞኑ ለሚገነቡ የመንገድ ሥራዎች 90 ሚሊዮን ብር ከማኅበረሰቡ መሰብሰቡን የሰሜን ሸዋ ዞን መንገድ መምሪያ ገለጸ።

102

ባሕር ዳር : ግንቦት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ሳሳው ጌታ እንዳሉት የማኅበረሰቡን የመንገድ ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ከሚያከናውነው የመንገድ ሥራ ባሻገር ባለፉት ዓመታት 51 ቀበሌዎችን በመለየት በማኅበረሰብ ተሳትፎ መንገድ እየተሠራ ይገኛል።

በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዞኑ ከ181 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ከ1 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር በላይ አዲስና የጥገና የመንገድ ሥራ መከናወኑን አቶ ሳሳው ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ 90 ሚሊዮን ብር ከማኅበረሰቡ የተሰበሰበ ሲኾን ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ከአጋር አካላት የተሰበሰበ ነው።

በዘጠኝ ወሩ ከተሠራው የመንገድ ሥራ 125 ኪሎ ሜትር መንገድ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በአዲስ የቆረጣ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 53 ኪሎ ሜትር በክረምትና በበጋ ወራት መደበኛ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ቀሪ 1 ሺህ 72 ኪሎ ሜትር በማኅበረሰቡ ተሳትፎና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ የጥገና ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት።

በዞኑ የመንገድ ግንባታ ላይ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ኀላፊው በቀጣይም በዞኑ በሚከናወኑ የመንገድ ሥራዎች ላይ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ለማስቀጠል እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ዞኑ በማኅበረሰብ ተሳትፎ መንገድ ሥራ በክልሉ ካሉ ዞኖች ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዝ የክልሉ መንገድ ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበበጎ ፈቃድ ደም የሚለግሱ ሰዎችን ቁጥር ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።
Next article“አኹን ላይ ተመሳሳይ ክፍተቶች እንዳይኖሩ ከሕገ-መንግሥቱ የዝግጅት ወቅት መማር ይገባል” የሕግ አማካሪ