
“አንድም ማሳ ጦም አያድርም” ግብርና ቢሮ
ባሕር ዳር : ግንቦት 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ በኩል መንግሥት ለላቀ ምርትና ምርታማነት በምርምር የላቁ ግብዓቶችን ከመጠቀም እስከ እርሻ ምካናይዜሽን ግብርናውን እያዘመነ እንደኾነ ይገልጻል።
በሌላ በኩል ደግሞ አርሶ አደሮች በየዓመቱ እየተባባሰ በመጣውና መፍትሔ በራቀው የግብዓት እጥረት እየተፈተንን ነው ይላሉ። በተለይ ዘንድሮ “ማሳችን ጦም የሚያሳድር ፈተና ተደቅኖብናል” እያሉ ይገኛሉ።
በአማራ ክልል የአርሶ አደሮቹ የአፈር ማዳበሪያ ጥያቄ ከግብርና ጣቢያዎች ወጥቶ የርእሰ መሥተዳደር ደጅ እስከመርገጥ ደርሷል። ከሰሞኑ የባሕር ዳርና አካባቢው አርሶ አደሮች ቀንበራቸውን ሰቅለው፣ከብቶቻቸውንና ማሳቸውን ትተው፣ ወደ ክልሉ ርእሰ ከተማ ባሕር ዳር በሰልፍ ገብተዋል። ተደራጅተው የበላይ ላሉት አካል የገጠማቸውን ችግር አቤት ብለዋል።
ከስርጭት መዘግየት እስከ ፍትሐዊነት ችግር መኖሩ ደግሞ “በእንቅርት ላይ…” እንዲሉ ኹኔታውን የከፋ አደርጎታል የሚለው የአርሶ አደሮች አቤቱታ ነው።
የአፈር ማዳበሪያ እጥረት፣የአርሶ አደሮች ስጋት፣የመንግሥት የመፍትሔ መንገድ የዘገባችን መዳረሻ ነው።
ግብርና ሚኒስቴር የአለፈው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳያገጥም አስቀድሞ ሥራዎች እንደሠራ ገልጿል ።ገና በታሕሳስ ወርም 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተገዝቷል፣ካለፈው ዓመት ተርፎ ያደረ ከተባለው ጋር ተዳምሮም 15 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል፣ይህም ለ2015/16 የምርት ዘመን በቂ እንደኾነ ሲገለጽ ቆይቷል።
ኾኖም የግብርና ሚኒስቴር የአስቀድሞ መረጃ ትንተናና ቅድመ ዝግጅት ጊዜው ሲደርስ ግን የአፈር ማዳበሪያውን ከአርሶ አደሮች እጅ እንዲገባ አስቻይ መፍትሔ አልኾነም።
የአፈር ማዳበሪያ እጥረቱ ምክንያት እንዴት ተፈጠረ? ፣የአርሶ አደሮቹ ጥያቄና መፍትሔውስ ምንድን ነው? አሚኮ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮን ጠይቋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው በሰጡት ማብራሪያ የአፈር ማዳበሪያ እጥረቱ ዘንድሮም እንደአምናው ሀገራዊ ችግር ነው ብለዋል።
በ2015/2016 የምርት ዘመን 150 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ያቀደው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣9ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልገኛል ብሎ ግዥ መጠየቁንም ከቢሮው ተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው አጀበ እንደሚሉት ክልሉ ለበጀት ዓመቱ ግዥ የተፈጸመለት የአፈር ማዳበሪያ ግን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
እስካሁንም ወደ ክልሉ ከገባው በወቅቱ ለአርሶ አደሮች አለመሰራጨቱ ለአርሶ አደሮችም የቅሬታ ምንጭ መኾኑ ልክ ነው ባይናቸው።
የተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር በወቅቱ አለመግባት በተለይም ባለፉት 2 ወራት የማጓጓዝ ሥራው መቆም ክፍተቱን ፈጥሯል ነው የሚሉት።
ያም ተባለ ይህ መሬቱን አለስልሶ ሰብሎን ለመዝራት የአፈር ማዳበሪያውን የሚጠባበቅ አርሶ አደር አፋጣኝ መፍትሔ ያሻዋል።
ታዲያ የክልሉ ግብርና ቢሮ ከበጀት ዓመቱ ምርታማነት ዕቅዱ እንዳይጎድል ምን የመፍትሔ መንገዶችን አዘጋጅቷል፣ የቀረበውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለማሰራጨት ምን ቸገረው ጥያቄያችን ነው።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው አጀበ ስንሻው እንሚሉት ችግሮችን ለመሻገር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው።
ወደ ክልሉ የገባው የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነትና በፍትሐዊነት እንዲሰራጭ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ቀድሞ በበጀት ዓመቱ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አይኖርም በሚለው መረጃ ክልሉ ከማዕከላዊ ወደ እሩቅ ወረዳዎችና ዞኖች በብዛት ማሰራጨት መጀመሩ የሥርጭቱን ፍትሐዊነት እንዳዛባውም ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ ችግሩን እየለዩ ማስተካከያ እየተደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ቢሮው ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎችም ከማዕከላዊ መጋዘን ከኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን 150 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በብድር በማቅረብ ማሰራጨት አንዱ የመፍትሔ መንገድ ስለማድረጉም ነው የሚያስረዱት አቶ አጀበ።
አሁን ላይ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ቆሞ የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሥራ መጀመሩም ሌላው ችግሩን ለመሻገር አስቻይ ኹኔታ ነው ብለዋል።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ወደ ክልሉ 350 ሺህ ኩንታል የአፈር ማደሰበሪያ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለፍጥነቱም ዩኒየኖች ላይ ሳይራገፍ ቀጥታ መሰረታዊ ማኀበራት እንዲወስዱትና በቀጥታም ለአርሶ አደሮች እንዲያሰራጩት ይደረጋል ነው ያሉት።
“በአፈር ማዳበሪያ እጥረት አንድም መሬት ጦም እንዳያድር ታስቦ እየተሠራ ነው” የሚሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው አጀበ ፣ወደብ ላይ ያለውን ማዳበሪያ በዘመቻ በፍጥነት የማድረስ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
በሥርጭት ችግር ውስብስብ ተግዳሮቶች ላይ የወደቀው የአፈር ማዳበሪያ ከችግሩ ተላቆ የአርሶ አደሮችም ጭንቀት እንዲፈታ በዋናነት የመንግሥትን የአሠራር ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ኾኗል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!