
የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ከሚኖሩ አማራዎች እና የአማራ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በአማራ ክልል ልማት እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው በዋሽንግተን ዲሲ፣ ቨርጂኒያ፣ ሜሪላንድ እና በልቲሞር ከሚኖሩ አማራዎች እና የአማራ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር የተወያዩት። በውይይቱም ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ በአማራ ጉዳይ እየሰሩ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ተሳትፈዋል።
የአማራ ጉዳይ ያገባናል የሚሉት ሁሉ በአንድ ጥላ ሥር ተሰባስበው እና ተናብበው በክልሉ ትርጉም ላለው ውጤት እንዲሰሩ አቶ ዮሐንስ ጥሪ አቅርበዋል። በሕዝቡ ሰላም እና ልማት ጉዳይ በኃላፊነት ስሜት በመሥራት የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉም ነው ተወያዮቹን የጠየቁት።
የአልማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ የአልማን የቀጣይ ሶስት ዓመታት የለውጥ ዕቅድ እና የሚከናወኑ ተግባራት በተመለከተ ለተወያዮቹ አስገንዝበዋል። በዕቅዱ ከአባላት፣ ከመንግስት እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ለመሰብለብ ከታቀደው 21 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ውስጥ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ አባላት በዓመት በአማካይ 120 ዶላር ለማግኘት እንደታሰበም አስረድተዋቸዋል።
ከአልማ ባሻገር በአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በንቃት እንዲሳተፉም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ያስገነዘቡት።
ክልሉን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በየጊዜው ተወያይቶ ከመለያዬት ያለፈ ቀጣይነት ያለው ተግባር ማከናወን እንደሚገባም ነው አቶ መላኩ የተናገሩት። በኢንቨስትመንት አማራጮች መሰማራት ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች መምከር እና ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባም ለተወያዮቹ አስረድተዋቸዋል፡፡ በዚህም ከራስ አልፎ ለሕዝቡ ህይወት መቀየር እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ለክልሉ ሕዝብ ኑሮ መሻሻል በሚሰሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ስር ተሰባስበው ለክልሉ ልማት እንዲሰሩም ለምሁራኑ፣ ለባለሀብቶች፣ ለሚዲያ አካላት እና ለማኅበረሰብ አንቂዎች የሥራ ኃላፊዎቹ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።
ምክክሩ በሜሪላንድ-ሲልቨር ስፕሪንግ ሲካሄድ የታደሙ ተሳታፊዎችም በተደራጀ መልኩ በአንድነት ለሕዝብ ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አማራውን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በሚያደርጉ አጀንዳዎች ላይ በትብብር እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጡት። አልማን በመደገፍም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መማር እንዲያበቃ አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ – ከሜሪላንድ