
ጎንደር፡ ግንቦት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞች በተሠራው የጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራ ከ83 ነጥብ 9 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን መምሪያው አስታውቋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና ልማት መምሪያ ለአምሥተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ መርኃ ግብር ልዩ ልዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
በከተማ አሥተዳሩም የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ጨምሮ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞች ማዘጋጀት መቻሉን የገለጹት በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የደን ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ትዛሉ አሰሙ ናቸው። በከተማው ውስጥ በሚገኙ 11 የገጠር ቀበሌዎች እስካሁን ከ150 ሺህ በላይ የችግኝ ጉድጓድ መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ አስቻለው ወርቁ፤ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ከልሎ ለማስጠበቅ እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
በዚህም በ2014 /15 የተተከሉ ችግኞች ከ83 በመቶ በላይ የጽድቀት መጠን መኖሩን ነግረውናል ። ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሀገር በቀል እና የውጭ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የገለጹት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አክናፍ አለሙ፤ በደን ልማት እንቅስቃሴ ውስጥም ማኀበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ ከ100 ሺ በላይ የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል ።
ችግኞች የሚተከሉበትን ቦታ ማዘጋጀት ለአረንጓዴ ዐሻራ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መካከል ወሳኝ ነው የሚሉት ኀላፊው፤ በዚህም መምሪያው የቦታ ልየታ ማድረጉን ተናግረዋል። ከ385 ሄክታር በላይ በደን ለማልማት መታሰቡን አክለው ገልጸዋል። ከሰኔ 15 ቀን 2015 ጀምሮ የዐረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለማስጀመር መታቀዱን የገለጹት ኀላፊው ለውጤታማነቱ የሁሉም ኅብረተሰብ ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!