የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ግን አለ?

311

ባሕር ዳር: ግንቦት 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የምንገኘው በ2015/16 የመኸር ምርት እርሻ እና የዘር ወቅት ላይ ነው፡፡ “አንድ ክረምት የነቀለውን 10 ክረምት አይመልሰውም” ይላል አርሶ አደር የክረምት ወቅት የቱን ያክል አስፈላጊ መኾኑን ሲያወሳ፡፡ በተለይ ደግሞ ሀገራዊ እድገት እና ምጣኔ ሃብታዊው መሠረቱ በግብርና ትከሻ ላይ ለተመሠረተባቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የመኸር ወቅት የተለየ ትርጉም አለው፡፡

በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የምርት መጠን የአማራ ክልል 40 በመቶውን ድርሻ ይሸፍናል፡፡ በዘንድሮው የመኸር የምርት ዘመንም ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በመኸር እርሻ በመሸፈን ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እንደታቀደ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ አኩሪ አተር እና ሩዝ የክልሉ ግብርና ቢሮ በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን ለመሸፈን ትኩረት የሰጣቸው ዘርፎች ናቸው ተብሏል፡፡

ክልሉ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እና ጸጋዎቹን በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው ያሉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ኃይለ ማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) በዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመንም 32 በመቶ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዷል ብለውናል፡፡

የታቀደውን ምርት እና ምርታማነት ለማሳካትም 40 በመቶው በኩታ ገጠም፣ 53 በመቶው ደግሞ በመስመር እና 850 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በግብርና ቴክኖሎጂ የሚዘራ እንደኾነ ነግረውናል፡፡

ይህንን ያክል ሀገራዊ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ያቀደ ክልል የግብዓት አቅርቦት ዝግጅቱ ምን ይመስላል የሚለውን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አለ የሚለው መነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ኾኗል፡፡ በተወሰኑ አካበቢዎችም አርሶ አደሮች የክረምት የእርሻ ዝግጅታቸውን አቋርጠው የአፈር ማዳበሪያ ፍለጋ እና አቤቱታ ሲመጡ ይስተዋላል፡፡ አሚኮ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ግን አለ? ሲል ለግብርና ቢሮ ኅላፊው ላቀረበው ጥያቄ ዶክተር ኃይለማርያም ምላሽ አላቸው፡፡

የማዳበሪያ ግዥ የሚፈጸመው በፌደራል መንግሥት ነው ያሉት ዶክተር ኃይለ ማርያም የፍላጎት እቅዱ ግን ከላይ ወደ ታች ከቀበሌ ወረዳ፣ ከወረዳ ዞን እና ከዞን ክልል የተዘጋጀ ነው ይላሉ፡፡ ክልሉ 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ለ2015/16 የምርት ዘመን ታቅዶ ለፌደራል መንግሥት ተልኳል፡፡ የፌደራል መንግሥት የክልሉን እቅድ ተቀብሎ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የማዳበሪያ ግዥ ፈጽሟል ነው ያሉት ኅላፊው፡፡

ለአማራ ክልል የሚያስፈልገው የመዳበሪያ አይነት ዩፒኤስ እና ዩሪያ የተባሉ የማዳበሪያ ዓይነቶች ናቸው ያሉት የግብርና ቢሮ ኅላፊው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ተጓጉዞ ወደ ክልሉ ገብቷል ብለዋል፡፡

ካለፈው ዓመት የከረመ 299 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እጃችን ላይ አለ የሚሉት ኅላፊው በጥቅሉ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ክልሉ ውስጥ አለ፡፡ ነገር ግን ይላሉ ዶክተር ኃይለ ማርያም እስከ አሁን ድረስ ለአርሶ አደሩ የተሰራጨው 41 በመቶ ብቻ ነው፤ ችግሩ ያለውም ከዚህ ላይ እንደኾነ ኅላፊው ያነሳሉ፡፡

ክልሉ ውስጥ ከከረመው እና በአዲስ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 96 በመቶ የሚኾነው የአፈር ማዳበሪያ ከዩኔኖች ወደ መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማኀበራት ተጓጉዟል፡፡

ክፍተቱ ከመሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማኀበራት ለምን ወደ አርሶ አደሮች አልተሰራጨም የሚለው ነው የሚሉት ዶክተር ኃይለማሪያም ሁለት መሠረታዊ ክፍተቶችን እንደ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ የፌደራል መንግሥት ለክልሉ ግዥ ከፈጸመው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ መጋቢት እና ሚያዚያ ላይ ሙሉ በሙሉ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ አልገባም፤ በዚህ ምክንያት 50 በመቶ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ አልደረሰም፡፡

ሁለተኛው ምክንያት በክልሉ ውስጥ ከከረመው እና በአዲስ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 96 በመቶው ወደ መሠረታዊ የኀብረት ሥራ ማኀበራት ተሰራጭቶ እያለ ለምን ወደ አርሶ አደሮች አልደረሰም የሚለው ነው የሚሉት ዶክተር ኃይለማርያም ይህ ክፍተት የወረዳዎች መኾኑን መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ከዞን እስከ ቀበሌ የግብዓት ስርጭት ኮሚቴ ተቋቁሟል የሚሉት ዶክተር ኃይለማርያም በእጃችን ያለው የአፈር ማዳበሪያ ለምን አልደረሰም የሚለውን መመለስ ያለበትም ኮሚቴው እንደኾነ ያነሳሉ፡፡

ክልሉ የአፈር ማዳበሪያ መጋዘን የለውም የሚሉት ኅላፊው ከፌደራል የሚመጣው ማዳበሪያ ወደ ዩኔኖች እና የኀብረት ሥራ ማኀበራት መድረሱን መከታተል እና ማረጋገጥ ሥራችን ነው ይላሉ፡፡ በሀገር ደረጃ ተፈጥሮ በነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ፌደራል ለክልሉ ማቅረብ የነበረበትን የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ አለማድረሱ ክፍተት መኾኑን አንስተው ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን መቅረብ የሚገባው ማዳበሪያ አልቀረበም ብሎ ለመጠየቅም በእጃችን ያለውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ሙሉ በሙሉ ማሰራጨት ነበረብን ነው የሚሉት፡፡

በ2015/16 የምኸር ዝግጅት ሁሉም አርሶ አደሮች ሁሉንም አዝርዕት በተመሳሳይ ወቅት አይዘራም የሚሉት ዶክተር ኃይለ ማርያም ያለውን ማዳበሪያ በእርሻ መርሐ ግብሩ መሠረት በፍትሐዊነት አሰራጭቶ ቀሪውን መጠየቅ ሲገባ ሁሉንም መካዘን ውስጥ አስቀምጦ የዘር ጊዜን ማሳለፍ ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡

ከሰሞኑ ቅሬታ በተነሳባቸው ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም እና አዊ አካባቢዎች የሚዘራው በቆሎ ነው የሚሉት ኅላፊው ለበቆሎ ዘር የሚበቃ የአፈር ማዳበሪያ አለ ይላሉ፡፡ ቀጣይ ጤፍ፣ ስንዴ እና ሌሎች አዝርዕቶችን ለሚዘሩ አርሶ አደሮች ደግሞ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሚጓጓዝ ስለሚኾን ተደራሽ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

አሁን ላለው የእርሻ ሥራ በቂ የአፈር ማዳበሪያ አለ፤ እሱን ለአርሶ አደሮች አሰራጭቶ ቀሪውን መጠየቅ ምክንያታዊነት ነው ነገር ግን አሁን ያለው የአፈር ማዳበሪያ ለሁሉም አርሶ አደሮች እና አዝርዕት አይደርስም ብሎ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ በመኾኑም በየደረጃው ያሉ የግብዓት ኮሚቴዎች መጋዘን ውስጥ ያለውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በፍትሐዊነት ማሰራጨት ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአገልግሎቱ ለእጀባ፣ ለበረራ ደኅንነት መኮንኖችና አመራሮች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን አስመረቀ።
Next articleየፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኀላፊዎች የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይን ጎበኙ።