
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ሂደት ውስጥ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ባለሙያዎች ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስገነዘበ።
ያለፈው አንድ ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስኬቶችና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረና ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የተሳተፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ተካሂዷል ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የሚኒስትሩ ተወካይ ዶክተር ሚልኬሣ ጃገማ በመድረኩ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአንድ ዓመት ጉዞ የተሳካ እንዲሆን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
ንቅናቄው ከመጀመሩ በፊት በአቅም ውስንነት፣ በግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዲሁም በመሬትና ፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች ምክንያት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ50 በመቶ በታች ነበር ብለዋል።
በንቅናቄው ለኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች በተደረገው የተቀናጀ የአቅም ግንባታ፣ የፋይናንስና የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ የማምረት አቅማቸው ከማደጉ ባለፈ ጥራት ያለውን ተኪ ምርቶች ማምረት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በጨርቃ ጨርቅ፣ በምግብና ምግብ ነክ፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ምርቶች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፈ ብዙ ድሎች መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
የመድረኩ ዓላማ ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶች ላይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ አግኝተው ቀጣይ ሥራዎች ላይ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በንቅናቄው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ መዘጋጀቱን የገለፁት ዶክተር ሚልኬሣ፤ ዘርፉ በተለይም በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የምርትና ምርታማነት ውጤታማነትና የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ሀገራዊ ራእይ ለማሳካት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በሙያቸው እንዲያግዙ ነው ብለዋል።
በተለይ በአግሮ ኢንዱስትሪዎች ያለውን የባለሃብቶች ተሳትፎ ለማጠናከር የሚደረገውን ንቅናቄ በሙያቸው ማገዝ እንደሚገባቸው በማከል።
በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚዲያ ሞኒተሪንግ ዴስክ ሃላፊ አቶ ካሣሁን መንግስቴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች በማጀብ ረገድ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በተለይም ንቅናቄው የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የተግባቦት ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የአቅም፣ የአቅርቦትና የፋይናንስ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ ከማስቻል አኳያ ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ያለፈው አንድ ዓመት የንቅናቄው ጉዞ እንዲሳካ የድርሻቸውን ማበርከታቸውን የገለፁት ሃላፊው፤ አሁንም የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ባለሙያዎች ሀገራዊ ራዕይ እንዲሳካ በሙሉ አቅማችን መስራት አለብን ብለዋል።
በተመሳሳይም የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተፈለገው መልኩ ወደ ሥራ እንዲገቡ በሙያችን ማገዝና መደገፍ አለብን ሲሉም ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ይህም ሀገራችን በቂ የኢንዱስትሪ ምርቶች እንድታመርት የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!