
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እና በዓባይ ባንክ መካከል የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ አጠቃቀም እና የብድር ሥርዓት መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የብድር ውል ሥምምነቱ ለእርሻ ቴክኖሎጂ ምቹ የኾነውን የክልሉን ግብርና በማዘመን በኩል ድርሻው የላቀ ነው ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ኃይለ ማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ክልሉ ካለው የእርሻ መሬት ውስጥ ከ42 በመቶ በላይ ለቴክኖሎጂ ምቹ ሥነ-ምህዳር ያለው ነው ብለዋል፡፡ ከሀገራዊ ምርት 40 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው የአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት የእርሻ ሥራው በበሬ እና ገበሬ ጫንቃ ላይ የተንጠለጠለ ነበር ተብሏል፡፡ ክልሉ ከ800 በላይ ያልበለጡ ትራክተሮች ያውም በውስን አካባቢዎች ለእርሻ ይጠቀም ነበር ያሉት ዶክተር ኃይለ ማርያም ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ የተሰራጨው የእርሻ ትራክተር መጠን 1 ሺህ 500 በላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
በክልሉ ለሚስተዋለው የእርሻ ቴክኖሎጂ እጥረት ሁለት ምክንያቶች ነበሩት ያሉት ኅላፊው የመጀመሪያው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ የአርሶ አደሩን ትክክለኛ አቅም መሠረት ያደረገ የፋይናንስ ሥርዓት አለመዘርጋቱ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተፈቅዶ በአራት ድርጅቶች ግዥ ተፈጽሟል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን እንዳያሳድግ ሌላኛው ማነቆ የነበረው የአርሶ አደሩን አቅም ያገናዘበ የፋይናንስ ሥርዓት አለመኖሩ ነበር የሚሉት ዶክተር ኃይለማርያም ይህንን ችግር ለመሻገር ዛሬ የውል ሥምምነት ከተፈራረምንበት ዓባይ ባንክ ተጨማሪ ፀደይ ባንክ፣ አማራ ባንክ እና ልማት ባንክ ጋር ስምምነት ተወስዶ አቅርቦት እየተፈጸመ ነው ብለዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማት የግብርና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ለማሟላት እያሳዩት ያለው ቁርጠኝነት የሚበረታታ ነው ያሉት ኅላፊው ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋርም አብሮ ለመሥራት ግብርና ቢሮ በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡
የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት መደገፍ የዓባይ ባንክ ማኅበራዊ ኅላፊነት ጭምር ነው ያሉት ደግሞ በዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የባሕር ዳር ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ ሲሳይ ፀጋየ ናቸው፡፡ ዓባይ ባንክ ከተመሰረተ 12 ዓመታት ብቻ ያስቆጠረ ባንክ ቢኾንም በመላ ሀገሪቱ እስከ ቀበሌ ድረስ 478 የሚደርሱ ቅርንጫፎች አሉት ያሉት ሥራ አሥኪያጁ ለአርሶ አደሩ በቅርበት መገኘታችን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ባንኩ የክልሉን ግብርና ለማዘመን ከዚህ ቀደምም በተለያዩ አገልግሎቶች ተሳታፊ እንደነበር ያነሱት አቶ ሲሳይ፤ አሁን የወሰድነው የውል ሥምምነት ግብርናውን ከማገዝ በዘለለ በባለቤትነት ለመሥራት እድል የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡ የብድር ሥምምነቱ ሌላ የንብረት ዋስትና ማስያዝ ሳያስፈልገው 20 በ80 ቀመር የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ 20 በመቶ አርሶ አደሩ ቆጥቦ 80 በመቶ ባንኩ በብድር የግብርና ግብዓቶችን ያቀርባል፡፡ የአርሶ አደሩን የመክፈል አቅም ያገናዘበ እና ከ7 እስከ 10 ዓመት የመክፈያ ጊዜ የተቀመጠለት እንደኾነም በውል ስምምነቱ ወቅት ተነስቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!