የክልሉ የወባ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡

309

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 16/2012ዓ.ም (አብመድ) ኢንስቲቲዩቱ ባለፉት ዓመታት በነበረው መረጃ ላይ ብቻ ተንተርሶ ዝግጅት ማድረጉ የመድኃኒት እጥረት እንዲያጋጥመው አድርጎ እንደነበርም ገልጿል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጄንሲ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት በቂ መድኃኒት ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት የክልሉ የወባ ስርጭት ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም በ2011 ዓ.ም ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የወባ ፕሮግራም አማካሪ አቶ ፀሐይ ተዋበ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ የክልሉ የ2011 ዓ.ም የወባ ስርጭት 7 ነጥብ 7 ነው፡፡ በተያዘው ዓመትም ጭማሪ ማሳየቱን ነው አቶ ፀሐይ የተናገሩት፡፡ በቅርቡ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የወባ መራቢያ ቦታዎች እየተስፋፉ መሆኑንና ስርጭቱም እስከ ታኅሳስ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ከኢንስቲቲዩቱ በተገኘው መረጃ መሠረት በ2010 ዓ.ም 280 የወባ ተጠቂዎች ሕክምና ተደርጎላቸዋል፡፡ በ2011 ዓ.ም ጨምሮ 301 ሺህ ሕሙማን በጤና ተቋም ሕክምና አግኝተዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም ጥቂት ወራት 216 ሕሙማን በበሽታው መጠቃታቸውን የተናገሩት አቶ ፀሐይ በዓመቱ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ ሊያሳይ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡

አጠቃላይ የክልሉ የወባ ተጠቂዎች ብዛት 201 ሺህ 600 መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ በሽታው በስፋት ምዕራብ አማራ በተለይም በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር፣ ምዕራብ ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም በአንዳንድ የምሥራቅ አማራ አካባቢዎች እየተስተዋለ መሆኑን ነው አቶ ፀሐይ የነገሩን፡፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ያነጋገርናቸው ሰዎች የወባ በሽታ በጥንቃቄ እጥረት ምክንያት እንደሚከሰት ነግረውናል፡፡ በዞኑ የአብርሃጂራ ከተማ ነዋሪው አቶ በላቸው ሙሉዓለም እንደነከሩን አካባቢው በርሃማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የወባ በሽታ ይከሰታል፡፡ እርሳቸውም ለተደጋጋሚ ጊዜ በወባ በሽታ መጠቃታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተያዘው ዓመትም አጎበር ባለመጠቀማቸው እና ከዚህ ቀደም በመንግሥት አማካይነት ይቀርብ የነበረው አጎበር ባለመቅረቡ ምክንያት ለወባ በሽታ መጋለጣቸውን ነው አቶ በላቸው የገለጹት።

አቶ ሀብታሙ ተሰማ የተባሉ ግለሰብ በአግባቡ አጎበር አንደሚጠቀሙ ነግረውናል፡፡ በዚህም እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ከወባ በሽታ ማዳን ችለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለሥራ ከደጋማ አካባቢዎች ወደ ቦታው የሚሄዱ የጉልበት ሠራተኞች የበሽታው ግንዛቤ ስለሌላቸው ጥንቃቄ እንደማያደርጉና ለበሽታው እንደሚጋለጡ ነው የተናገሩት፡፡
ያለፉት ዓመታት የስርጭት መቀነስ የተፈጠረው መዘናጋት በኅብረሰተሰቡ ‹ወባ የለም› የሚል አስተሳሰብ እንዲኖር ማድረጉ፣ አጎበርን በአግባቡ አለመጠቀምና የአየር ሁኔታው ለወባ መራባት ምቹ መሆን ለስርጭቱ መጨመር በምክንያትነት ተነስተዋል፡፡ በሽታው ከተገመተው በላይ በመከሰቱ የመድኃኒት እጥረት ተከስቶ ስለነበር የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመመጣጠን እንደተከሰተም ተናግረዋል፡፡

ቀደም ብሎ የነበረው የመድኃኒት እጥረት መቀረፉን ደግሞ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጄንሲ አስታውቋል፡፡ በኤጄንሲው የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሳሉ ጫኔ በዚህ ጊዜ 42 ሺህ የወባ ታማሚዎችን ማከም የሚያስችል በቂ መድኃኒት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡ ተጨማሪ 600 ሺህ ሰዎችን ማከም የሚያስችል መድኃኒት ወደ ቅርንጫፉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል የመድኃኒት እጥረት እንደነበር የተናገሩት አቶ አምሳሉ በሽታው በፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ መድኃኒት በአስቸኳይ ትዕዛዝ እየተገዛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ከክረምቱ መግባት ቀደም ብሎ በቂ የአጎበር ስርጭት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ የመሳሰሉ ስሜቶች የወባ መሽታ ምልክቶች በመሆናቸው ይህ ምልክት የሚታይባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሕክምና ምርመራ አድርገው በ24 ሰዓታት ውስጥ መድኃኒት መውሰድ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ አጎበሮችን በአግባቡ መጠቀም፣ ውኃ ያቆረባቸውን ቦታዎች ማፋሰስ፣ የወባ መከላከያ የተረጨባቸውን ቤቶች አለመለቅለቅ እና የወባ ትንኝ የሚራባበትን ቦታ ማዳፈን እንደሚገባም መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

Previous articleበክልሉ ከ4 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ተሰብስቧል፡፡
Next articleበውጭ ሀገራት የሚኖሩ አማራዎች በተቀናጀ መልኩ ለክልሉ ልማትና ሰላም እንዲሰሩ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ አቀረቡ።