“በጤናው ዘርፍ በማኅበረሰቡ አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

83

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጤናው ዘርፍ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚሰተዋሉ የአስተሳሰብና የአመለካከት ችግሮች ተገቢውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ተግዳሮት እንደኾኑ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው የኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ከዓመት ዓመት እያደገ ቢመጣም አሁንም የአመለካከትና የአስተሳሰብ ዝንፈቶች እንዳሉ ነው።

እናም በአማራ ክልል በጤናው ዘርፍ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ያስችላል የተባለለት ፕሮጀክት በባሕር ዳር ይፋ ተደርጓል።

በመድረኩ እንደተገለጸው “ዩኤስ ኤይድ ሔልዚ ቢሔቬርስ አክቲቪቲ” በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በክልሉ ለአምስት ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክት ነው ይፋ የተደረገው።

ፕሮጀክቱ በእናቶች ጤና፣ በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር፣ በኮሮና ቫይረስ እና በቤተሰብ እቅድ ላይ የሚሠራ ነው ተብሏል።

በፕሮጀክቱ የማስተዋወቅ መድረክ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ እንደተናገሩት ቢሮው በጤናው ዘርፍ ከሚሠሩ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ነው፣ለዚህ ፕሮጀክት ስኬታማነትም በቁርጠኝነት እንሠራለን ነው ያሉት።

“በጤናው ዘርፍ በማኅበረሰቡ አመለካከትና አስተሳሰብ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋልም” ብለዋል ምክትል ቢሮ ኀላፊው አብዱልከሪም።

ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃም በጤና ዘርፍ ዙሪያ የኅብረተሰብ አስተሳሰብና አመለካከት ላይ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር ፣ኅብረተሰቡንም በጤና አገልግሎት የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ታላሚ አድርጎ የሚሠራ ፕሮጀክት ስለመኾኑ የተናገሩት ደግሞ የፕሮጀክቱ ምክትል ኀላፊ ህብረት ጌታነህ ናቸው።

ሥራው በዩኤስ ኤይድ ድጋፍ የሚከናወን ፕሮጀክት መኾኑን የተናገሩት ምክትል ኀላፊዋ የሚስተዋሉ አጉል ልማዳዊ ድርጊቶችን ማረም፣ግንዛቤን ማሳደግና ጥሩ ተሞክሮዎችንም ማስቀጠል ላይ በትኩት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

ለሚከናወኑ አስቻይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም የማኅበረስብ ውይይት አንደኛው መንገድ ነው ተብሏል። በፕሮጀክቱ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች የሚሳተፉ ሲኾን የለውጥ ሞዴል ቤተሰቦችን በምሳሌነት እንደሚጠቀሙም ነው ያስረዱት።

ለፕሮጀክቱ ስኬታማነትም በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ተባባሪ እንዲኾኑ አሳስበዋል።

ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል በ6 ዞኖች፣ በ31 ወረዳዎች የሚተገበር ነው ተብሏል።

በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ክፍተቶች ተገቢውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ተግዳሮት እንደኾኑም ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ችግሮችን ለመቅረፍ አልሞ የተነሳው ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲኾንም የድርሻችን እንወጣለን፣ በቅንጅትም እንሠራለን ብለዋል።

በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ጤና ዘርፍ ኀላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ በሚደረገው መልሶ ማቋቋምና ግንባታ በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከዓባይ ባንክ በክልሉ ትራክተርን ጨምሮ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ተፈራረመ፡፡