
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስትራቴጅ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ከተገባ አንደኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡
በአማራ ክልል በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት የኦፕሬሽን ዘርፍ አስተባባሪ አየነው በላይ (ዶ.ር) እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰቱ ጦርነቶች 50 በመቶ የሚኾነው ጉዳት የደረሰው በአማራ ክልል ነው፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በክልሉ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ፎረም ጋር በመቀናጀት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት፣ በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተፈጠሩ ግጭቶች የደረሰው ጉዳት በጥናት መለየቱን ገልጸዋል፡፡
የሱዳን ኀይሎች በምዕራብ ጎንደር ዞን በኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሃብቶች ላይ ያደረሱት ጉዳትም አንዱ የጥናቱ አካል ነው፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው በክልሉ የሚገኙ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳትም ጥናቱ አካትቷል፡፡
በተደረገው ጥናት በክልሉ አጠቃላይ 522 ቢሊዮን ብር የሚደርስ መሠረተ ልማት መውደሙን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ከንብረት ውድመት ባለፈ በርካቶች መገደላቸውን፣ በሴቶች ላይ የመደፈር፣ የመደብደብ እና የሥነ ልቦና ጉዳት መድረሱንም አንስተዋል፡፡
በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋምና ለመገንባት የአምስት ዓመት የሃብት አሰባሰብ ስትራቴጅክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ከገባ ዓመት አስቆጥሯል ነው ያሉት፡፡
በ2015 ዓ.ም ረጂ ድርጅቶች እና የክልሉ መንግሥት በመደበው በጀት የመልሶ ግንባት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ዶክተር አየነው የነገሩን፡፡ በበጀት ዓመቱ የክልሉ መንግሥት በመደበው 1 ቢሊዮን ብር ከፍተኛ ውድመት በደረሰባቸው ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ የመጠጥ ውኃ ተቋማት በመሳሰሉ የዘጠኝ ተቋማት ግንባታ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ እንደሚጠናቀቁም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
በተለይም ደግሞ በጦርነቱ ጊዜ የተደፈሩ ከ2 ሺህ 300 በላይ ሴቶች ኑሯቸውን ሊያሻሽል በሚችል የገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የዓለም ባንክ በሀገሪቱ በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች ከመደበው 300 ሚሊዮን ዶላር 50 በመቶ በክልሉ ሰባት ወረዳዎች ትግበራ እየተካሔደ እንደሚገኝም ዶክተር አየነው አንስተዋል፡፡ በቀጣይ በጀት ዓመትም በተመረጡ አስራ ሦስት ወረዳዎች ላይ በሚገኙ 348 ቀበሌዎች እንደሚሠራ ለአብነት ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት ፈንድ ጽሕፈት ቤቱ በቀጣይ ዓመታት የተለያዩ የሃብት ማፈላለጊያ ዘዴዎችን በመጠቀም የሃብት ማሰባሰብ ሥራውን እንደሚሠራ ነው ያብራሩት፡፡ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባለፈ ማኅበረሰቡን፣ ረጅ ድርጅቶችንና የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ በስፋት ለማሳተፍ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸውልናል፡፡
በውጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ረጅ ድርጅቶች ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ በማድረግ የክልሉን ልማት እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!