በክልሉ ከ4 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ተሰብስቧል፡፡

318

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 16/2012ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል የሚገኙ በርካታ ባለሀብቶችና ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ ታማኝ ግብር ከፋዮች ተብለው ተሸልመዋል፡፡ ዕውቅናም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ታማኝ ግብር ከፋይ ከሆኑ ሰው ጋር ቆይታ አድረገናል፡፡ የአዲናስ አጠቃላይ ሆስፒታል በሀገር አቀፍ ደረጃ በታማኝ ግብር ከፋይነት ሽልማት የተበረከተለት ድርጅት ነው፡፡ ሐሳባቸውን ለአብመድ የሰጡት የሆስፒታሉ ከፊል ባለሀብትና ኃላፊ መኩ ዳምጤ (ዶክተር) “ሕግን አክብረን ስለሠራን ተሸላሚዎች ሆነናል” ብለዋል፡፡

ግብር ግዴታ ነው የሚሉት ዶክተር መኩ ማንኛውም ግብር ከፋይ መረጃን በጥራትና በትክክለኛነት በመያዝ የሚጠበቅበትን መክፈል አለበትም ብለዋል፡፡ ግብር ካልተከፈለ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር ላይ እንደሚወድቅ የተናገሩት ዶክተሩ ግብር ከፋዩ ትክክለኛ መረጃን በመያዝ ትክክለኛውን ግብር መክፈል እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡ ትክክለኛውን የሒሳብ አያያዝ ከተያዘ ትርፉና ኪሳረው ስለሚታወቅ ግብር ለመክፈልም አመቺ ይሆናል ነው ያሉት ዶከተር መኩ፡፡

በድርጅታቸው ውስጥ ያለው የሒሳብ አሠራርና የግዥ አፈጻጸም ትክክለኛና ሕጉን የጠበቀ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ትክክለኛ ሥራ ለሠሩበት መከፈል የሚገባውን ብቻ እንደሚከፍሉም ነው የተናገሩት፡፡ በገቢዎች በኩል መመሪያዎችን በወቅቱ የማድረስ ክፍተት እንዳለ ያመላከቱት ዶክተር መኩ መመሪያውን በወቅቱና በጊዜው በማድረስ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ማፍራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ አዲናስ ጠቅላላ ሆስፒታል ከደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች አንዱ ነው፡፡

በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰን አሰባበሰብና ክትትል ዋና የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ ይታይህ ፈንቴ በክልሉ በሦስቱም ደረጃ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብይታቸውንና ገቢያቸውን አሳውቀው ግብር የሚከፍሉበት ወቅት ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 2012 ዓ.ም እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል 18 ሺህ 289 የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች እንዳሉ የገለጹት አቶ ይታይህ 14 ሺህ 579 ግብር መክፈላቸውን አስታውቀዋል፡፡

የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮችም 79 በመቶ የሚሆኑት እንደከፈሉ ነው የገለጹት፡፡ በክልሉ የግብር አከፋፈል ሂደት ኦዲት ተደርጎ ዝቅተኛ ገቢ ማስመዝገብ፣ የሒሳብ መዝገብ አለመያዝና የደረሰኝ አጠቃቀም ችግሮች እንዳሉ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ የሚታዩ ክፍተቶችን ቢሮው ቴክኒካዊ የሆኑ አሠራሮችን በመጠቀም እንደሚሞላና የቀረውን ክፍያ እንደሚያስከፍልም ተናግረዋል፡፡ በደረጃ “ሐ” 97 በመቶ እና በደረጃ “ለ” ደግሞ 78 በመቶ የሚሆኑት ያለ ቅጣት እንደከፈሉም አስታውሰዋል፡፡ ቢሮው ታማኝ ግብር ከፋዮችን እንደሚያበረታታ የገለጹት አቶ ይታይህ መመሪያን በማድረስ በኩል ያለውን ክፍተትም ወደፊት እንቀርፋለን ነው ያሉት፡፡

በገቢ አሰባሰብ በኩል ያለውን የሕግ መጣስ ለመቆጣጠር ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሠሩ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ የሚስታዋለውን ሕገ ወጥ ንግድ ለመቆጣጠርም ከክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ እንደደረሱም አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ገቢና ከከተማ አግልግሎት በአጠቃላይ 14 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ከግብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ነው፡፡የሕዳር ወር አፈጻጸምን ሳይጨምር በተደረገው አሰባሰብ ሂደትም 4 ነጥብ 266 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉ ታውቋል፡፡ የኦዲት ሥራው በደንብ ሲሰራ ገንዘቡ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችልም ተገልጧል፡፡ በዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው የግብር ገቢም 39 ነጥብ 1 በመቶው ተሰብስቧል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleበዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጅ ባለሀብቶች በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎታቸውን ገለጹ።
Next articleየክልሉ የወባ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡