
ባሕር ዳር: ግንቦት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በነበራቸው የቻይና ቆይታ የአማርኛ ትምህርት አሰጣጥ እና የመጽሐፍ ምረቃ ላይም ታድመው እንደነበር ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አቶ ደመቀ ከግንቦት 15 እስከ 20 በቻይና ጉብኝት አድርገዋል።
እንደቃል አቀባዩ ገለጻ ጉብኝቱ የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ያሳደገ ነው። እንደሚታቀው የአሁኑ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደሥልጣን በመጡ ጊዜ የመጀመሪያቸውን ጉብኝት ያደረጉት በኢትዮጵያ ነው ብለዋል።
ወደ ቻይና ያቀኑት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጉብኝታቸው በጓንዡ ትልቅ የኢንቨስትመንት ውይይቶች አድርገዋል። በዚህ ውይይት ላይ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የልማት ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያጠናክሩ የተደረገ ውይይት መኾኑን ተናግረል።
ለቻይና መንግሥትም ኢትዮጵያ ለባለሃብቶቹ የምትታመን እና አስፈላጊ ወዳጅ ሀገር መኾኗን ገልጸዋል።
ባለሃብቶቹም በኀይል አቅርቦት ዘርፍ፣ በኢንፎርሜሽን፣ በቴክኖሎጅ እና በግብርና ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ ኢምባሲ መርቀው የከፈቱ ሲኾን ኢምባሲው እንደሀውልት ቆሞ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የሚያጠናክር ነው ሲሉ ቻይናውያን ዱፕሎማቶች መግለጻቸውንም አንስተዋል። የኢትዮጵያን ኢምባሲ የአፍሪካ ቤት ነው ያሉት ቃል አቀባዩ የአፍሪካ ኹነቶች የሚከወኑበት መኾኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት በባሕል እና በቋንቋ እያደገ የመጣ ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም አማርኛ ትምህርት በቻይና ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ነው። ይህንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ተገኝተው መጎብኘታቸውን ገልጸዋል። ተማሪዎቹ አማርኛን አቀላጥፈው የሚናገሩ፣ ግጥም የሚያነቡ ለመመረቅ የደረሱ ተማሪዎች ናቸው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታተሙ 3 መጽሐፍት ምረቃ ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ መታደሙን አምባሳደር መለስ አብራርተዋል።
ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!