
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጣና ሐይቅ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ በረከት ነው። ከኢትዮጵያዊያንም አልፎ የዓለምን የአየር ጸባይ ለውጥን በማመጣጠን ለምድራችን ጤና አስፈላጊ ሥለመኾኑ ታምኖበት በዓለም አቀፍ መዝገብ የሰፈረ ሕይወት አድን ሃብት ነው። የሁሉም ሃብት የኾነው ጣና የተለመዱ እና ተጨማሪ አዳዲስ በረከቶችን እየለገሰ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ፣ ጸጋዎቹም የበለጠ እንዲበዙ ከተፈለገ ከተደቀነበት የኅልውና አደጋ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል።
የአማራ ክልል ጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ.ር) በጣና ሐይቅ ዙሪያ የተደቀኑ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ የኅልውና አደጋዎችን በርካታ ናቸው ብለዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በየዓመቱ ከ30 ሜትሪክ ቶን በላይ ደለል ወደ ሐይቁ እየገባ በዓመት ብቻ እስከ 10 ሴንቲ ሜትር የሚኾን የሐይቁ ክፍል ከወለሉ ተነስቶ ወደ ላይ በአፈር እየተሞላ ስለመኾኑ በጥናት ተረጋግጧል።ይህ የሐይቁን ጥልቀት እና የውኃ መጠን የሚቀንስ ሲኾን በሕልውናው ላይ ትልቅ አደጋ ነው።
ከከተሞች እየወጣ ወደ ሐይቁ የሚለቀቅ ፍሳሽ ቆሻሻ ሌላው በጣና ላይ የተደቀነ አደጋ ነው። ጎንደር እና ባሕርዳርን ጨምሮ በዙሪያው የሚገኙ ሌሎች አነስተኛ ከተሞችም ፍሳሽ ቆሻሻቸውን ያለከልካይ ወደ ሐይቁ ይለቃሉ። ይህ ቆሻሻ ወደ ሐይቁ ገብቶ እንደማዳበሪያነት በመዋል ለመጤ አረሞች ምቹ ኹኔታን ይፈጥራል ተብሏል።
ዶክተር አያሌው ሐይቁን ያለበቂ ጥናት መጠቀም ሌላው የጣና የኅልውና አደጋ ነው ብለዋል። ለአብነትም በከተሞች አካባቢ ጣና ውስጥ አፈር እና ድንጋይ በማስገባት እና በመደልደል ለማልማት የሚደረጉ ሙከራዎችን አንስተዋል። በተለይም በባሕርዳር ከተማ በርካታ የሐይቁ የውኃ ዳርቻዎች በባለሃብቶች አማካኝነት እየተደለደሉ ይገኛሉ ነው ያሉት። ኤጀንሲው ይህንን ለማስቆም ጥረት እያደረገ ቢኾንም በሌሎች አስፈጻሚ አካላት በኩል የሚታየው ቸልተኝነት ግን ችግሩ እንዲቀጥል አድርጎታል ነው ያሉት።
“ጣናን የሚጋፋው በዝቷል” ያሉት ዶክተር አያሌው ከጣና ጸጋዎች ለመጠቀም የሚጥር እንጅ የሐይቁን ኅልውና ለመጠበቅ የሚሠራ አካል እየጠፋ ስለመኾኑ አንስተዋል። ሐይቁን በሚያዋስኑ ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የሐይቁን የውኃ ዳርቻ ተከትለው ለማረስ ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። ይህ ተግባር ከቅርብ ርቀት የሚነሳ ከፍተኛ ደለል ወደ ሐይቁ እንዲገባ የሚያደርግ እና ውኃውንም የሚያደርቅ በመኾኑ የየቀበሌዎች የሥራ ኀላፊዎች ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባቸው ዶክተር አያሌው ተናግረዋል።
በከተማዎችም በርካታ ሆቴሎች በዙሪያቸው ያለውን የጣና ውኃ መጠበቅ ሲገባቸው ይልቁንም ከሐይቁ ገላ ቁራሽ መሬት ለማግኘት ሲባል ወደ ውኃው አፈር እና ድንጋይ በማስገባት እና በመደልደል ላይ ተጠምደዋል። ይህ የሚፈጸመው በየከተሞች አሥተዳደር መሪዎች ዕውቅና ጭምር በመኾኑ ችግሩን ለመከላከል አዳጋች እንዳደረገው ዶክተር አያሌው ተናግረዋል።
እንዲህ አይነቱ ሐይቁን ያለአግባብ እና በስግብግብነት የመጠቀም ልማድ ካልተወገደ በስተቀር የጣና ኅልውና የበለጠ ስጋት ውስጥ እንደሚወድቅ ተመላክቷል። ጣና በጥፋት እጅ ለመንካት የሚደፈር ሳይኾን በስስት ሊታይ እና ሊጠበቅ የሚገባ የሀገር ሃብት ነው። ስለዚህ ጣና ከትውልዶች ጋር ሁሉ አብሮ እንዲኖር “ከሐይቁ ምን ልጠቀም” ከማለት ጎን ለጎን “እንደምን ልጠብቀው” የማለት ባሕልን ማካበት ግድ ይላል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!