
ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን ከ508 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የብርዕና አገዳ ሰብሎች ዴስክ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ቢረዳ እንደገለጹት፤ በፌዴራል ደረጃ በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን በኩታገጠምና በመደበኛ ግብርና ከሚሸፈነው 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ508 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡
እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ በዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል። እንደ ሀገር በተመረጡ 12 ሰብሎች ላይ የኩታ ገጠም ሥራ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ በመኸር ምርት ዘመን ከ16 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በሰብል ምርት ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል።
እንደ ኢፕድ ዘገባ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎች ላይ ትኩረት በማድረግ በኩታገጠም እርሻ እንዲለሙ ይደረጋል ሲሉም ገልጸዋል። በተለይም በተግባርና በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የሚሠሩ ሥራዎች በዝርዝር ተቀምጠው ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት አቶ ፍቃዱ። በመኸር ምርት ዘመን ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ ይለማል ብለዋል፡፡
እንደሀገር በክላስተር ከሚለማው መሬት ብቻ ከመኸር ምርት ከ299 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አቶ ፍቃዱ አስታውቀዋል። በክላስተር የሚለማው ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ባለፈው ዓመት የነበረውን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የክላስተር ልማት ወደ 8 ነጥብ 5 ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ግብዓት በወቅቱ ለማቅረብ፣ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ፣ የክህሎት ሥልጠና ለመስጠት፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማቅረብና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በክላስተር፣ በመስኖና ፣ በኩታ ገጠም የሚመለማውን መሬት ለተገቢው ጥቅም ለማዋል በፌዴራልና በክልሎች አስፈላጊው ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል። በባለፈው የመኸር ምርት ዘመን 13 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን 394 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማምረት መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!