
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 15/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በጎንደር ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የፓርቲው ደጋፊዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ በፓርቲው ርዕዮተ ዓለምና በዚህ ወቅት በአማራ ሕዝብ ብሎም በሀገሪቱ እየደረሱ ስላሉ ችግሮች በስፋት ተነስቷል።
አዴኃን ከትጥቅ ትግል መልስ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በቻለው አቅም ሁሉ እየሠራ ስለመሆኑ ተናግሯል፣ አሁንም የሕዝቡ የኅልውና ችግር የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ ለመታገል መደራጀት ሁነኛ መፍትሔ ስለመሆኑም ተጠቅሷል።
ሕዝቡ ያልተመለሱለትን ጥያቄዎች ለማስመለስም ሆነ የአማራ ሕዝብ ያልተወከለበት ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ለማስደረግ በፖለቲካዊ አቅሙ ተገዳዳሪ የሆነ አደረጃጀት እንደሚያስፈልግም ተጠቅሷል፤ ፓርቲዎች በተቻለ መልኩ አንድ ሆነው የሚታገሉበትን መንገድ መፈለግ እንዳለባቸውም በውይይ ተጠቁሟል።
አዴኃን ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ስለመቆየቱ የጠቀሱት ተወያዮቹ አሁንም ከሌሎች የክልሉን ሕዝብ ጥቅም ለማስበር ከሚታሉ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ በመቀጠል መሥራት እንደሚገባው ተመላክቷል።
በጎንደር ሲኒማ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ በፅናት ትግል የማድረግ ተገቢነትም ተነስቷል። የአማራ ሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለማስገኘት ብስለት በታከለበት የፖለቲካ አካሄድ ያለመታከት መታገል እንደሚገባ ነው የተገለጸው። ለዚህ ደግሞ ወጣቶችም ወደ ውጤታማ የትግል ስልት እንዲገቡ ተከታታይ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው የተነገረው።
አዴኃን ምሁራንን ይበልጥ እያሳተፈ መሥራት እንደሚገባውም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ -ከጎንደር