
ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ረቡዕ ገበያ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የስናን ወረዳ ከተማ ናት። ከ30 ሽህ በላይ ሕዝብ ይኖርባታል። ከደብረ ማርቆስ ከተማ 27 ኪሎ ሜትር ወደ ሰሜን አቅጣጫ ከጮቄ ተራራ ግርጌ ትገኛለች። ጮቄ “የውኃ ጋን” የሚለውን ግዙፍ ስም ይሸከም እንጅ ጋኑን ተደግፈው የከተሙ የረቡዕ ገበያ ከተማ ነዋሪዎች ግን ተጠማን ብለዋል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ወደ ረቡዕ ገበያ ተጉዞ የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ተመልክቷል። ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት ውኃ የምትመጣው በወር አንዴ ብቻ ነው። እንደመጣች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሳ የምትጠፋዋን ውኃ ለማግኘት በሚደረግ የተራ ግብግብ አላስፈላጊ ማኅበራዊ ችግር ውስጥ እየገቡ ስለመኾኑም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ነዋሪዎች በሌሊትም ጭምር በአካባቢው ወደሚገኙ ወንዞች በመውረድ አማራጭ የመጠጥ ውኃ እየፈለጉ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል። ይህም ለከፍተኛ እንግልት እና ለውኃ ወለድ በሽታዎች አጋልጦናል ነው ያሉት።
ከተማዋን እና የጮቄን የውኃ ማማነት የሚመጥን ንጹህ የመጠጥ ውኃ ተገንብቶ ችግራቸው እንዲቀረፍም ጥያቄ አቅርበዋል።
የረቡዕ ገበያ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ነብዩ ሙሉ ከተማዋ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች ብትኾንም የንጹህ መጠጥ ውኃ እጦት እየፈተናት ነው ብለዋል። ረቡዕ ገበያ ከተማ 30 ሽህ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ብትኾንም የውኃ አቅርቦት ችግር የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ስለመኾኑም አቶ ነብዩ ገልጸዋል።
አቶ ነብዩ እንዳሉት ነዋሪዎች ለክልሉ መንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የ305 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ በ2012 ዓ.ም ግንቦት ላይ የውኃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሮ ነበር። ከከተማው 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 28 ሊትር በሰከንድ የሚያመነጭ ውኃ ቁፋሮ መካሄዱንም ተናግረዋል። ጉድጓዱ ከተቆፈረበት ቦታ እስከ ከተማው ድረስ ውኃውን እየተቀባበሉ የሚገፉ አራት የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታም ከተጠናቀቀ ዓመት ተቆጥሯል። ይሁን እንጅ በወቅቱ በነበረው ሀገራዊ ጉዳይ ምክንያት የቱቦ ቀበራው እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ሳይጠናቀቅ በመቋረጡ ጋኖቹ ውኃ አልባ ናቸው፤ የከተማው ነዋሪዎች የመጠጥ ውኃ ችግርም ተባብሶ ቀጥሏል።
የተቋረጠው የረቡዕ ገበያ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ በ2015 ዓ.ም እንደገና እንደሚቀጥል የክልሉ ውኃ ቢሮ አቅጣጫ ያስቀመጠ ቢኾንም ወደ ተግባራዊ ሥራ ግን አልተገባም። ተገንብተው የተጠናቀቁ ጋኖችም በቶሎ ውኃ የማይጠራቀምባቸው ከኾነ ለብልሽት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አቶ ነብዩ ጠቁመዋል። በቶሎ ቱቦውን በመዘርጋት ውኃ እንዲይዙ በማድረግ ከፍተኛ ወጭ የተከፈለባቸውን ጋኖች ከብልሽት መታደግ እና የነዋሪዎችን የመጠጥ ውኃ ጥያቄ መፍታት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተስፋየ አባቡ በበኩላቸው የከተማውን የውኃ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ታስቦ በ2012 ዓ.ም የተጀመረው ፕሮጀክት የተቋረጠው በበጀት ችግር ምክንያት ስለመኾኑም አንስተዋል።
የተቋረጠውን የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ቱቦ ለመዘርጋት ብቻ 210 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል። በ2015 ዓ.ም በክልል ደረጃ ለቢሮው የተበጀተው በጀት 650 ሚሊዮን ብር ሲኾን ከዚህ ላይ ለአንድ ወረዳ ብቻ 210 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረግ አስቸጋሪ ስለመኾኑ አቶ ተስፋየ ገልጸዋል። በሚቀጥለው ዓመት በጀት ተይዞለት ሥራው እንደሚጀመርም ተናግረዋል።
ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እስከሚያገኝ ድረስ በአካባቢው የምንጭ ማጎልበት ሥራ ተከናውኖ ነዋሪዎች ጊዜያዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል። ለዚህም ቢሮው ለሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲሁም አስፈላጊውን የቱቦ እና ተያያዥ ቁሳቁሶች ግዥ ፈጽሞ በቅርብ ቀናት ውስጥ ለወረዳው እንደሚያስረክብም አቶ ተስፋየ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!