ድርቅ ያላደረቃቸው ለምለሞች፡

215

የሚትጎለጎል አውሎ ነፋስ ጋር እየታገለች ወደ መንደሯ ስትቃረብ ማዶ ማዶ ሲያዩ የነበሩ ልጆቿ እየሮጡ ጉልበቷ ስር ተወሸቁባት፡፡ የተሸከመችው 50 ሊትር የሚይዝ ቢጫ ጎማሙሉ ውኃ ከቅርብ የመጣ መስሏቸዋል፡፡ ወገቧ ቢብረከረክም ጎንበስ ብላ ከመሳም ሌላ አማራጭ የላትም መሰለኝ በደስታ እየተፍለቀለቀች በየተራ ልጇቿን እያሻሸች ስማ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
የመጀመሪያ ልጇ ጋሻው ከ50 ሊትሩ በላይ በቀኟም በግራዋም እያፈራረቀች የምትይዘውን ቅጠል ተቀብሎ ከትክሻው ላይ አድርጎ ውሏቸውን እየነገራት ነው፡፡ “አሁን እኔ እናታችሁ ምን የመሠለ መቆያ እሠራላችኋለሁ እሺ” ስትላቸው በደስታ ብርሃን ፊታቸው እየበራ፤ የእናታቸውን ናፍቆት ተወጥtው በተደጋጋሚ በረጅሙ ይተነፍሳሉ፡፡
ልጆቹ ትኩር ብለው እየተመለከቱኝ መምህር ወይም ግብርና ባለሙያ መስያቸው እንደ ቤተሰብ ‹ጋሼ ጋሼ› ይሉኛል፡፡ መምህራንና የግብርና ባለሙያዎች በየአካባቢው በቅርበት ስላሉ ከልጆች ጋር በቀላሉ ይላመዳሉና፡፡ እኔም ‹‹እንዴት ናችሁ?… ጎበዞች! …› እያልኩ ለጥያቄዎቻችሁ ምላሽ ያልትን እየሰጠሁ ቀጠልኩ፡፡ ከቤታቸው አጠገብ ስንደርስ ‹‹በዚህ ነው›› አሉኝ፡፡ ይህን ጊዜ ነው ይዘዋቸው የዋሉት አያታቸው በንዴት እየጦፉ ማዶ ማዶውን እያዩ ‹‹በቃ እኔን ተዋችሁኝ ማለት ነው!›› ሲሉ የሰማኋቸው፡፡
ልጆቹም ‹‹አይ… አይ… አይ…›› እያሉ ሊያስረዷቸው ሁላቸውም በየፊናቸው ምክንያታቸውን ይደረድሩ ጀመሩ፡፡ ‹ከእናታችሁ እና ከአያታችሁ ማንን ትወዳላችሁ?› ሲባሉ አብረው ከሆኑ ‹ሁለታችሁንም ነው› ብለው ድርቅ ይላሉ፡፡ ለየብቻቸው ከሆኑ ግን የዋዛ እንዳይመስሏችሁ፤ ‹አንቺ ነው የምንወድሽ፤ እሷ እንዳይከፋት ብለን ነው እኮ› እያሉ እያንዳንዳቸውን ያባብሏቸዋል፡፡ ልጆቹን ሲንከባከቡ የቆዩት አያት ልጃቸውን ‹እንደምን ዋላችሁ ስላስዋ ምነው ዘገያችሁ?› አሉ፡፡ ቀኑ ለእርሳቸው ምቹ ሆኖ ልጆቹም ያላስቸገሯቸው ቀን ‹ዛሬስ ቶሎ መጣችሁ› ቀኑ ካልተመቻቸው ደግሞ ‹ዛሬስ ምነው ዘገያችሁ?› እንደሚሉ ልጃቸው ነግራኝ ነበርና በውስጤ ፈገግ አልኩ፡፡
የአማቷ ቤት እና የነስላስ ቤት ፊት ለፊት ሆኖ መካከሉ ለእንስሳት ማደሪያ የሚሆን ቦታ እንዳለ የጋጡ ሽታ እና ያልተጠረገው ኩበታቸው በራሱ ይናገራል፡፡ ከደጃፉ አንድ በማሽላ አገዳ የተሠራ ዳስ አለ፡፡ ከጠፍር የተሠሩ ሁለት አልጋዎች በዳሱ ውስጥ እና ከአማቸቸው ቤት አጠገብ ይታያሉ፡፡ አልጋዎቹን የበግ እና የፍየል ግልገሎቹ ከፊሎቹ ከላይ ወጥተው ከፊሎቹ በአልጋ ሥር ሆነው የራሳቸው ያደረጉት ይመስላሉ፡፡
አማቻቸው ድንገት እንደሚያውቁኝ ሁሉ ሰፍ ብለው ‹‹ውይ እንዴት ዋልክ?›› ብለውኝ ስላስን ጎማዋን ሳያወርዱ ቀድሞ ለእኔ ማረፍያ እየፈለጉ ‹‹ቺት ቺት›› እያሉ ግልገሎችን አባረው ከዳሱ ሥር የታጠፈውን ምንጣፍ ገልብጠው አንጥፈው እንድቀመጥ ጋበዙኝ፡፡ ምንጣፉ ላይ በቁሜ ልወድቅ ብየ በራሴ አፈርኩ፡፡ አይ የከተማ ሰው ሻንጣ ተሸክሜ ይድከመኝ? ከስላስ ጋር እራሴን ሳነፃፅር በዕድሜም በአካልም ብበልጣት ነው እንጅ አላንስም? ግን እርሷ ያንን ሁሉ መንገድ 50 ሊትር ውኃ ተሸክማ መጥታ ሳታወርድ እኔ ለመቀመጥ ቸኮልኩ፡፡
ስላስ ጎማውን አውርዳ በአመድ የተዳፈነውን ምድጃ በእንጨት ገፋ ገፋ አድርጋ እሳት ማያያዝ ጀመረች፡፡ ስላሳ ድቡልቡል ድንጋይ በቀኝ እጇ ይዛ ቋንጣ ከጠፍጣፋው ወፍጮ ላይ እያደቀቀች ነው፡፡ በጎን እሳቱን እፍ እያለች በብረት ምጣድ ቡና ታጥባለች፡፡ የመጨረሻ ልጇ ጎልበቷ ሥር በጎን ተወሽቆ ይጠባል፡፡ አማቻቸው በኽምጠኛ ቋንቋ ‹‹ሲጝን›› ከሚባል ኩሽና ቤት እንጀራ እየጋገረች ይመስላል፤ ምጣዱ ኰሽ ሲል እና የእንጀራው ሽታ ይደርሰኛልና፡፡ ማገዝ ባለመቻሌ ውስጤን ያብከነክነኛል፡፡
ማዶ አሻግሬ ሳይ ድርቁ ረጅም ርቀት ለሰዓታት ተጉዘው ውኃ እንዲቀዱ ብቻ ሳይሆን ዛፎች ላይ ቅጠል እንዳይኖር አድርጎ የእንስሳትን ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ እንዲያም ሆኖ የእንስሳት ተዋፅዖ የቀነሰባቸው አይመስልም፡፡ ጋሻው መጥቶ ከሐሳቤ ሲነጥለኝ ‹ብዙ ፍየሎች አሏችሁ?› አልኩት ግልገሎችን ዓይቼ መገረሜ ነው፡፡ ‹‹አይ ጋሼ ድሮ ነው እንጂ በሦስት አራት እረኛ የሚጠበቁት፤ አሁንማ በተደጋጋሚ ድርቅ እየተከሰተብን በአንድ እረኛ ቤት ላይ ማደር ጀመሩ አይደል›› አለኝ፡፡ ሀብት ሲበዛ ከመንደሩ ራቅ ባለ ዋሻ ወይም ምቹ መጠለያ ያለው ጋጥ ላይ ማሳደር የአካባቢው ባሕል እንደሆነ ሲነግሩኝ ከሰማሁት ጋር አስማማሁት፡፡
‹‹ጥጆቹን ጠብቆ ወተት በሳምንት ሁለት ቀን ጥዋት ላይ የሚቀበል ነው›› ያሉኝ አንድ ልጅ ‹‹ጥጆቻችሁን ተቀበሉ›› ብሎ ግቢ አስገብቶ ሌሎችን እየነዳ ሄደ፡፡ ስላስና ልጃቸው ጋሻው ግልገሎቹ እና ጥጆቹ ከወላጆቻቸው ጋር ተገናኝተው ላሞች እስከሚታለቡ ድረስ ወደየማደሪያቸው ሲያስገቡ ዓይቼ ልረዳቸው ብነሳም እንግድነቴን ያወቁ ይመስል ስለበረገጉብኝ ተቸገርኩ፤ ልጆቹ በሁኔታዬ ሲሳሳቁብኝ በእንስሳቱ ተናድጄባቸው ተመልሼ ወደ ማረፊያየ ሄድኩ፡፡
ብርሃኑ ተሸንፎ ጨለማው ተራ ይዟል፡፡ በእንስሳት ጥበቃ፣ በአካባቢ ጉዳይ የሚመክሩ፣ ማሳ ላይ የነበሩ ሁሉ ከየዋሉበት እየተመለሱ ስለሆነ እኔም ሁሉንም በየተራ ‹እንዴት ናችሁ?›› እያልኩና ማንነቴን እየነገርኳቸው አሁንም ሌላ ሥራ ስላላቸው መጣን እያሉኝ ይሄዳሉ፡፡ ስሃላ ሰየምት መንደረ ጨርቆስ ቀበሌ ከጨለማ ጋር ከጀመረችው ትግል በላይ ልጆቻቸውን የሚጠሩ ላሞች እና ፍየሎች፣ እናቶቻቸውን ከሚናፍቁ ግልገሎች እና ጥጆች በተጨማሪ የበሬ ጩኸት እና የሙክቶች ድምፅ ጎልቷል፡፡ አንዳንዴ ከእነዚህ ድምፆች ሌላ በየመካከሉ የውሾች ድምፅ እና የመንደሬው ሰዎች ‹እገሌ! ኧረ እገሌ› እየተባባሉ ከእንስሳት በልጦ ሊደመጥ በሚችለው ድምፅ በገደል ማሚቶው እየታገዙ ‹ወይ› ‹እንደምን ውለሃል?› ምስጢር አልባ ጣጣቸውን ለሁሉም ይነግራሉ፤ ዋናው መግባባቱ ነው፡፡ ይሄ ብዙዎች የሚያደርጉት እንደሆነም ቀንም አይቻለሁ፤ አንዱ ሲጣራ ሌላው በገደል ማሚቶ አማካኝነት አቤት ባይልም መስማቱ አይቀርም፡፡
እኔ ያለሁበት የእነ ስላስ ቤት ሁሉንም ሥራ ለመጨረስ እስከ ምሽቱ 4፡00 ሳይወስድባቸው አልቀረም፡፡ ስለአከባቢው ድርቅ ላናግራቸው ሄጄ ግን ጊዜ አላገኙም፡፡ ሁላቸውም ተሰባስበው ለመዓድ ቁጭ ስንል ስለከተማ ሕይወት ይጠይቁኛል፤ እኔም ስለእነሱ ሕይወት፣ ስለ ድርቁ ክስተት ስጠይቅ ስቀዳ አመሸሁ፡፡

ሊነጋ ሲል የሚንኳኳ ድምፅ ሰምቼ በሰመመን ነቅቼ ለማየት ብሞክርም አልተቻለኝም፡፡ ግን በአህያ ካሬታ ላይ የተጫነ ጎማ እንደሆነ አልተጠራጠርኩ፤ ውኃ ሊቀዱ ነው፡፡ ትናንት ወደ መንደረ ጨርቆስ ስመጣ ያጋጠመኝን ፀሐይ እና የፊቴ እንደዚያ መቀያየር አስቤ የአካባቢውን ሰዎች ብርታት ዓይቼ በራሴ አፍሬ ነበር፡፡ የአካባቢው ሙቀት በተለይ በመጋቢትና ሚያዝያ ወራት እስከ 38 ዴግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደሚደርስ ሰምቻለሁ፡፡
ትንሽ እንደቆየሁ ስላስ አሁንም የየዕለት ሥራዋን የምትጀምርበት ሰዓት ነው፡፡ እኔም የምፈልገውን መረጃ ስላገኘሁ ወደ ስሃላ ሰየምት ዋና ከተማ መሸሀ ተመልሼ ማደር እንዳለብኝ ማታ ነግሬያቸዋለሁ፡፡
ከመሸሀ፣ ዝቋላ ወረዳ ፅፅቃ ከተማ፣ ከፅፅቃ ከተማ ሰቆጣ ከተማ፣ ከሰቆጣ ወልዲያ፣ ከወልዲያ ባሕር ዳር የምደርስበት ቀን ብዙ ነው፡፡ የዕድል ጉዳይ ሆኖ በቀን አንድ ጊዜ በመንግሥት መኪና ከላይ ሆኖ መሄድ እንደመታደል ነው፡፡ የትራንስፖርት ጉዳይ በአዕምሮየ እየተመላለሰ ቢረብሸኝም ትራንስፖርት ያለበት ቦታ ላይ መድረስ ደግሞ ጉዳዩን ግማሽ ያደርሰዋል፡፡ ስላስ እንደዚያ በጢስ ስትታፈን ሳይ ቁርስ ልትሠራልኝ መሆኑን ገምቼ ጥዋት ቁርስ መብላት እንደማልወድ ነግሬ እንድንሄድ ብቻ ጠየቅኳቸው፡፡ ‹‹ካልክ እሽ …›› ብለው እርጎ ካልጠጣህ ብለው ሲማፀኑ ሳይ ምነው በእነዚህ ላይ ተደጋጋሚ ድርቅ ፀናባቸው ብየ አምርሬ እንዳዝን አደረገኝ፡፡
ያም ሆኖ ነጋ፤ እኔም ብዙ ዓመት እንደማቃቸው ሁሉ ችግራቸው ሲቃ እየተናነቀኝ ፤ ‹ለእነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ በድርቅ መጠቃት መንግሥት እንዴት መፍትሔ አጣ!› እያልኩ ሐዘንና ትካዜ በዝቶብኝ ልሰናበታቸው አቅም አጣሁ፡፡
ስላስ ከጀርባዋ አንድ ቢጫ ጀሪካን እና ሌላ በእጇቿ እያፈራረቀች የምትይዘውን ቅጠል በጀርባዋ ይዛለች፡፡ ዛሬ አህያቸው ገለባ ከመሸከም አርፎ ውኃ ሊያመጣ ሁለት ትልልቅ እና አንድ ትንሽ ጀሪካን በመጫኛ ተሸብልሎ ከፍት ከፊታችን ሰበር ሰካ ይላል፡፡ ትንሽ ኮረብታማውን መንገድ እንደሄድን አንድ ጊዜ ሳት ያለሰው ራሱን በማያገኝበት ገደል ሊወድቅ ስለሚችል በጥንቃቄ በእጅና እግራችን እየዳህን መውረድ ጀመርን፡፡ ጎልበታችን በይበልጥ የሚፈተንበት ነው፡፡ ቅጠላቸው የደረቁ ዛፎች ብቻ ናቸው ያሉት፤ ሳር የሚባል ነገር ለማየት ይቸግራል፡፡
ሁለት ሰዓት ያክል ተጉዘናል፤ እኔ ወደ መሸሀ ከተማ እሷ ወደ ወራጅ ወንዝ ልንሄድ ነው፡፡ ፀሐይዋ እንዴት ትለበልባለች መሰላችሁ፡፡ ብዙ ውኃ የሚቀዱ እናቶች ልጆች በመንገድ ላይ ተቀላልቅለውን መንገዱ በጀሪካን ጓጓታ ድምጽ ተሞልቷል፤ ደስተኞች ናቸው፡፡ የከፋኝ የሚመስለኝ እኔ ነኝ፡፡ ደግሞ የእኔን ሻንጣ ሊያግዙኝ ይዳዳሉ፡፡ ‹አረ በፈጠራችሁ!› በእነሱ ድካም እየተብሰከሰኩ ትርጉም አልባነቴን ሊነግሩኝ መሠለኝ ‹ጋሼ ከየት ነው የመጣህ?› እያሉኝ ለግማሹ ስላስ ለግማሹ እኔ እነግራቸዋለሁ፡፡
ስላስ እንደነገረችኝ ውኃ ቀድተው ለመመለስ ከስድስት ሰዓታት በላይ ይወስዳል፡፡ በተለይ ፀሐዩ በበረታበት ጊዜ ሰፋፊዎቹ የመሸሀ ከተማ ሸለቆዎች ከጥቋቁር ድንጋዮች እና ከሚፋጀው አሸዋ የሚወጣው እንፋሎት አቅልን ያስታል፤ ወበቅ ነው፡፡ ከዚህ ነፋሻማ አየርን መናፈቅ ቅዥት ነው፡፡ ቆየት ባለ ቁጥር ከነፋሻማ አየሩ ይልቅ እየተግተለተለ የሚመጣው አውሎ ነፋስ እያንገዳገደ ከነጎማቸው ሊወስዳቸው ይታገላል፡፡ ዓይናቸውን በአቧራ ሞልቶ ከገደሉ ሕይወት በተጨማሪ ፈተና ነው፡፡
ስላስ ገና በ27 ዓመቷ ሦስት ልጆች አሏት፤ አሁንም አለማርገዟን እንጃ፡፡ ልጆቿን መንከባከብ እና ሌላ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከማምጣት ይልቅ የዕለት ውኃ ማምጣት ብቻ ነው ጊዜ እና ሕይወትን የምታሳልፈው፡፡ ከሦስት ሰዓታት በላይ ከወሰደው የእግር ጉዞ በኋላ እኔ መሸሀ ከተማ ደርሼ እነ ስላስ ግን ከተማውን በዳር ትተው ወደ መሸሀ ወንዝ ሄዱ፡፡
ወደ ቀየው ስገባ ሻንጣየን ለማስቀመጥ ከተዋወቅኳቸው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ቤት ትቼ ከሱቅ ለእነ ስላስ ቤተሰቦች ቡና እና ስኳር ገዝቼ ወደ ወንዙ አመራሁ፡፡ ወንዙ ትልቅ እና ከራስ ደጀን ተራራ የሚነሳ ኩልል ያለ ውኃ ነው፡፡ የስሃላ ሰየምት ዋና ከተማ መሸሀ ነዋሪዎችም ለ9 ዓመታት ያክል ውኃ ቀድተው የሚጠጡት ከዚህ ወንዝ ብቻ ነው፡፡ ስላስን አግኝቼ በፌስታል የተቋጠረውን ዕቃ ስሰጣት ደንግጣለች፡፡ ላለመቀበል ብትጥርም እንደምንም ለምኜ ሰጥቻት ስልኬን ለባለቤቷ ስለሰጠሁ ስልክ ሲያገኙ እንዲደውሉልኝ በተደጋጋሚ ነግሬ ተለየሁ፡፡ ከዚህ ወረዳ ላይ ሁሉም ዕርዳታ ጠያቂዎች ናቸው፤ በትንሹ ያላቸው ነገር ይህ ነው ብሎ በድፍረት ለመናገር የሚያስችል ማሳያ የለም፡፡ ድርቁ ሰብላቸውንም እንስሶቻቸውንም እየቀማቸው ነውና፡፡
ከሁለት ወራት በኋላ የስላስ ባለቤት ደውሎልኝ ነበር፡፡ ከመንደረ ጨርቆስ ወደ ፈፋ ድልድይ አካባቢ መስፈራቸውን ነገረኝ፤ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ‹ምነው ያ ይሸላል?› አልኩት፡፡ ጥያቄያቸውን ይዤ እስከ ክልል ባለስልጣናት ተናግሬ ‹በቅርቡ ምላሽ እንሰጣለን› የሚሏትን መልስ ምን ብየ ልንገረው! ድንገት ግን የስላስ ባለቤት ‹‹አሁን ምን ዓይነት ጥሩ ቦታ መሠለህ የሠፈርነው!›› ብሎ ከድንጋጤ አወጣኝ፤ ‹‹የመኪና መንገድ አለው፣ ውኃ ከግማሽ ሰዓት እርቀት ነው፣ መንግሥት እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርት ቤት እከፍታለሁ ብሎናል፤ ጤና ኬላው ወደ ጤና ጣብያ ሊድግልን ነው፤ ወፍጮ ተተክሏል፤ ብቻ ከድሮው አንጻር ዓለም ነው›› አለኝ፤ በአጭር ጊዜ ይህ ሁሉ መሆኑ ደነቀኝ፡፡ ያ ሁሉ ጊዜ ውኃ ለማምጣት የሚጠፋውን ጊዜ ሳስብ አዲሱ የፈፋ ድልድይ ከችግር የተገኘ መፍትሔ ዘላቂ እንዲሆን ተመኘሁ፡፡
ከአምስት ዓመታት በኋላ አብመድ የእነ ስላስን አዲሱን ከተማ ፈፋ ድልድይ ተመልክቷል፡፡ አካባቢው ከዚህ በፊት የፍየል መዋያ ከመሆኑ ሌላ ምንም ነገር እንዳልነበረው አስታውሳለሁ፡፡ መና ወንዝም ዳሩ ከአቧራ ውጭ ሌላ አልበቀለበትም ነበር፤ ዛሬ ግን ጅምር የመስኖ ሥራዎችን አየሁ፤ አንዳንዶቹማ ሳይቀጥፉት አይቀሩም፡፡ ቀጥታ የሄድኩት ለስላስ ባለቤት ደውየለት ወደቤታቸው ነበር፤ በመኪና ነበር እስከ ቤታቸው የሄድነው፡፡ እንደቤተሰብ ተሳስመን ተገናኘን፡፡
አይ ስላስ ሁለት ልጆች ጨምራለች! ዛሬ ፊቷ ላይ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት እና በሥራ ባካኝነት አይታይባትም፡፡ ሁላቸውም የሆነ ችግር እንደተቀረፈላቸው የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡ ከተማዋ ገና በመንሠራራት ላይ ያለች በመሆኑ በቆርቆሮ ቤቶች የተሠሩ እንዳሉ ሁሉ በእንጨት ግድግዳዎች እና በጥቋቋር ኬንዳዎች የለበሱ ቤቶችም ይታያሉ፡፡ የሚገርመው ፕላናቸውን ጠብቀው ስለተሠሩ ለአካባቢው መጪውን የመሠረተ ልማት ግንባታ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡
መንገዱ ከስሃላ ሰየምት መሸሃ ወደ ጓህላ የሚወስድ የጠጠር መንገድ በመሆኑ ወደ ባሕር ዳር ለመሄድ አራት ቀናት መውሰዱ ተረት ሁኖ በግማሽ ቀን ነው የደረስነው፡፡ ወይ ጊዜ እንደእኔ አላያችሁትም፡፡ የፈፋ ድልድይ ከተማ በ2008 ዓ.ም ድርቅ ወቅት የተፈጠረች ናት፡፡ ሜዳ ናት፤ በጣም ለማደግ የሚያስችል አካባቢ ላይ የሰፈረች፡፡ ዛሬ በየተራራው ከነበሩ መንደሮች የመንግሥት ባለሙያዎች ተሰባስበው ከ1ኛ አስከ 8ኛ ክፍል ትምህርት ቤት አለ፤ ጤና ጣብያ አለ፡፡ ይሁን እንጂ ዘመኑን አልዋጁም፡፡
እነስላስን ጨምሮ ከተለያዩ ተራራማ ቀበሌዎች ወደ ፈፋ ድልድይ ወርደው የሰፈሩ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች አሉ፡፡ ልጆቻቸው ዛሬም በዳስ ላይ እንዲማሩ ተገድደዋል፡፡ ጤና ጣብያው ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፤ የባለሙያዎች እጥረትም አለ፡፡ ከቤታቸው አቅራቢያ ንፁህ መጠጥ ውኃ ለማስገባት የተደረገው ጥረት በብልሽት ምክንያት ቆሟል፡፡ 2008 ዓ.ም ሲሰፍሩ ጀምሮ የሚጠይቁት ሞባይል ኔት ወርክ አለመኖር መረጃ ለመለዋወጥ እና ለወሊድ እናቶችን ወደተሻለ ሕክምና ለማድረስ ፈተና እንደሆነ ነው፡፡ ዘንድሮ በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ መንግሥት የላከውን አስቸኳይ ድጋፍ ከመንደራቸው እየተረዱ የሚገኙት የፈፋ ድልድይ ነዋሪዎች ዘላቂ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎቻቸው አለመመለሳቸው ከተራራማ ቦታ ከመኖር የተለየ ነገር እንዳይኖር እያደረገ ነው፡፡
በአካባቢው አሁንም ድርቅ በመከሰቱ የወረዳው አስተዳድር ወደ ፈፋ ድልድይ ለሚሰፍሩ ዜጎች ቅድመ ዝግጅቶች ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የብሔረሰብ አስተዳድሩ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኘ መብራት ከድርቁ ጋር በተያያዘ መንገድ ባላቸው አካባቢዎች ላይ በተሽከርካሪዎች የውኃ ቦቲ በማስቀመጥ ችግሩን ለመፍታት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ የፈፋ ድልድይ የውኃ ፕሮጀክት እንደሚሠራ ነው የማውቀው ያሉት አቶ ተገኘ ወረዳው ችግሩን ባያሳውቅም በዕቅድ ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርጉ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
የብሔረሰብ አስተዳድሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ገብረሕይወት አዱኛ እንደተናሩት ፈፋ ድልድይ ላይ ከ2009 ጀምሮ ደረጃውን የጠበቀ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት ለተቋራጮች እና ለአካባቢው ኢንተርፕራይዞች ቢሰጥም በዋጋ ችግር አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርት ቤቱ ሥራ መጀመር አልቻለም እንጂ ቆርቆሮ ተመትቶ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ላይ ደርሷል፡፡ የወረዳው አስተዳድር ማጠናቀቂያ የቀረውን የትምህርት ቤቱ ግንባታ አካል ለሦስተኛ ወገን ሰጥቶ አስጨርሶ ሥራ እንዲያስጀምረ አቅጣጫ መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡ ፈፋ ድልድይ በትምህርት ዘርፍ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተጨማሪ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አማካኝነት የሚገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታም ጥቅምት መጨረሻ አካባቢ የሚጀመር በመሆኑ ችግሩ በቅርብ ጊዜ የሚፈታ እንደሆነ ምክትል ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
‹‹ፈፋ ድልድይ ከተማ ላይ የተገነባው ጤና ጣብያ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተስርቶ ሥራ ጀምሯል›› ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳድሩ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞገስ መርካ ናቸው፡፡ የእናቶች የወሊድ እና የማቆያ ክፍሎቹ ሙቀትን የሚቋቋሙ ማቀዝቀዥዎች የተገጠሙላቸው ናቸው ያሉት አቶ ሞገስ የሰው ኃይል እጥረትን ወረዳው እንዲያሟላ መግባባታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የሕክምና መሣሪያዎች እና መድኃኒቶች እንዲሟሉ ግን ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትዩት ጋር ዕቅድ ተይዞ ለመፍታት ፍላጎት መለዬቱ ነው የተገለጸው፡፡
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የሚጠየቀውን የሞባይል ኔት ወርክ አለመኖር ደግሞ የምሥራቅ አማራ ዲስትሪክት በተያዘው ዓመት ለመፍታት እቅድ መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleበኩር ጋዜጣ ህዳር 15-03-2012 ዓ/ም ዕትም
Next articleአዴኃን ከሌሎች የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ከሚታገሉ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ተቀራርቦ የመሥራት ጅማሮ እንዲያጠናክር ተጠየቀ፡፡