
ባሕር ዳር: ግንቦት 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የግብርና አፈጻጸምን በማሻሻል የምግብ ሥርዓትን የሚያሻሽል ብሔራዊ ኮንፈረንስ እያተካሄደ ነው።
በኮንፈረንሱ ላይ ሀገር አቀፍ እና ዓለምአቀፍ ምርምሮች ቀርበው ይገመገማሉ።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪው ሽመልስ አይናለም (ዶ.ር) ኮንፈረንሱ ሀገሪቱ በፖሊሲ ደረጃ ቀርጻ ያስቀመጠቻቸውን እቅዶች መሠረት አድርጎ እየተካሄደ መኾኑን ተናግረዋል።
ኮንፈረንሱ ሰብል ልማት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ እንስሳት እና ዓሣ ሃብት፣ የተፈጥሮ ሃብት ልማት አጠባበቅ፣ የዱር እንስሳት እና ሥነ መሥህብ የተመለከቱ አምስት አጀንዳዎች እንዳሉትም ተናግረዋል።
ከግምገማው በኋላ የተመረጡ ምርምሮች በተለያዬ መንገድ ለማኅበረሰቡ የሚደርሱበት መንገድ ይመቻቻል ብለዋል ዶክተር ሽመልስ።
ኮንፈረንሱ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች ድጋሚ ተሠርተው የገንዘብ፣ የጉልበት እና የጊዜ ብክነትን እንዳያመጡ ለማድረግ አንዱ ምክንያት መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ትምህርት ክፍል ተመራማሪው እንየው አድጎ (ፕሮፌሰር) አፈር በጎርፍ እየተጠረገ በርካታ አካባቢዎች ከማምረት ወጥተዋል። እነዚህን አካባቢዎች ወደ ቀደመ ኾኔታቸው ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) በሚቀጥሉት ዓመታት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋጋጥ እንደሚገባ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዚህ ዓመት በተሠራ ሥራ በየዓመቱ ኢትዮጵያ ለስንዴ ግዥ ታወጣ የነበረውን 1 ሚሊዮን ዶላር ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በኮንፈንሱ ላይ የተለያዩ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት እየተሳተፉ ሲኾን በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የተመረጡ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በውይይቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) እና የሌሎች ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ጥናት አቅራቢዎች እየተሳተፉበት ነው።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!