
ደብረ ታቦር ፡ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በቅርቡ በተሠራው የፖሊስ ሪፎርም መሰረት ወደ ኮሚሽኑ የተቀላቀሉትን የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላትን አሰልጥኖ አስመርቋል።
ወደ አማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የተቀላቀሉ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በዓለም በር ፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ነው ዛሬ የምረቃ ሥነሥርዓታቸው የተከናወነው።
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂ የፖሊስ አባላት እንደተናገሩት “ዛሬም እንደትላንቱ ለሀገርና ለሕዝብ ዋስትና በመኾን በተመደብንበት ተልዕኳችንን በብቃት እንወጣለን” ነው ያሉት።
ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ በቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አደረጃጀት ውስጥ ኾነው ሀገርንና ሕዝብን ከገባበት ችግር ለማውጣት መስዋዕት በመክፈል፣አኩሪ ጀብዱ በመፈጽም ብቃታቸውን እንዳሳዩ ነው ያስረዱት።
በቀጣይም በሚኖራቸው አዲስ አደረጃጀት የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ በብቃት እንደሚወጡም ገልጸዋል።ለዚህም ስልጠናው በብቃት ተልዕኮን ለመወጣት የሚያስችል እንደኾነም ነው የተናገሩት።
በቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አደረጃጀት የፈጸምነውን ታሪክ በመድገም ፣ምስጉን ስማችንም የምናስቀጥል ይኾናል ብለዋል ተመራቂዎቹ።
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ስልጠናውን አስመልክቶ ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ረዳት ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ታሪክ የማይረሳው አበርክቶ ሲፈጽሙ የነበሩ መኾናቸው አውስተዋል።
በአዲስ በተሠራው የፖሊስ ሪፎርም መሰረት የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንን በፍላጎታቸው ለመረጡ የቀድሞው የልዩ ኃይል አባላት የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የሚጠይቀውን አስቻይ ሙያዊ ስልጠና ወስደዋል ብለዋል።
የስብዕና ግንባታ፣የማረሚያ ቤት ደንብን ፣እጀባና ጥበቃ፣የማረምና ማነጽ ተግባርና መስል ስልጠናዎችን በመውሰድ ሰልጣኞች ተገቢውን ስብዕናና ክህሎት እንዲጨብጡ ተደርጓል ነው ያሉት።
ሰልጣኞቹ ከዚህ ቀደምም በነበሩበት አደረጃጀት ሰፊ ልምድ ያካበቱ፣በብዙ ፈተናዎች ያለፉ ናቸውና ለቀጣዩ ተልዕኳቸውም የማይበገሩ ይኾናሉ ብለን እንናምናለን ብለዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው ሁሌም ቢኾን በጸጥታው ዘርፍ ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት፣ለስኬታማነት ለውጥ ፣ መልሶ መደራጀትና ለላቀ ተልዕኮ መዘጋጀት የማይቋረጥ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ የፀጥታ መዋቅሮች በመረጡት ዘርፍ ለላቀ ግዳጅ እንዲዘጋጁ የማድረግ ሥራውን አስመልክቶ ቢሮ ኀላፊው እንደተናገሩት የዛሬ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ተመራቂ የፖሊስ አባላት በቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አደረጃጀት ስምሪታቸው የአማራ ሕዝብ እና ሀገር የገጠማቸውን የኅልውና ስጋት በላቀ ተጋድሎ በስኬት የተወጡ፣ የሕይወት መሥዋዕትነት ጭምር በመክፈል ያደረጉት አስተዋጽኦ ታሪክ የማይዘነጋው ነው ብለዋል። “እናንተ በሕዝብ ልብ ታሪካችሁን የጻፋችሁ ጀግኖች ናችሁ” ብለዋቸዋል ቢሮ ኃላፊው ደሳለኝ ጣሰው።
በብዙ ውጣውረድ ያካበቱትን ጀግንነትና ልምድ ዛሬም እንደ ትናንቱ በተሰማሩበት የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ለሚከናወኑ ተግባራት ተደማሪ አቅም በመኾን የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም የሥራ መመሪያ ሠጥተዋል።
ዘጋቢ :-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!