የሀገር ዋልታና መከታ የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስም ማጠልሸት መቆም እንዳለበት የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች አስገነዘቡ።

690

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ዋልታና መከታ የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስም ማጠልሸት መቆም አለበት ሲሉ የደቡብ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አድማሱ ዓለሙ አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በአዳማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የደቡብ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አድማሱ ዓለሙ እንዳሉት መከላከያ የማንም የፖለቲካ ውግንና የለውም የኢትዮጵያ ሕዝቦች መከታና ጋሻ ነው።

”እኛ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያለአንዳች ልዩነት እኩል የምናከብር፣ ኢትዮጵያን በክብር እያገለገልን ያለን የሀገሪቷ የመጨረሻ ምሽጎች ነን” ብለዋል።

ይህም በመኾኑ በተለያየ መንገድ የሀገር ሉዓላዊነት ምልክት የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስም ማጠልሸት ሊቆም ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

”ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች የተደረገልን የድጋፍ ሰልፍ ተልዕኳችንን በብቃት እንድንወጣ ተጨማሪ አቅምና ሞራል የሚሆነን ነው” ያሉት ሜጄር ጄኔራሉ በዚህም ሠራዊቱ ለሕዝቡ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና አለው ብለዋል።

በተመሳሳይ ዘገባ የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በሸገር ከተማ በኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል። “የሀገር መከታ የኾነውን ሠራዊት በመበተን ሀገርን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሠሩ ወገኖች ሀገራቸው ፈርሶ የሚንከራተቱን አይተው ልቦና ሊገዙ ይገባል” ብለዋል።

መከላከያ ሠራዊት ከማንኛውም ፖለቲካ ገለልተኛ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ሹማ፣ ሕዝቡ በምርጫ ያስቀመጠውን መንግሥት የመጠበቅ ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታውን ብቻ እንደሚወጣ ገልጸዋል።

ከዚህ በማለፍ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ጥንቃቄ ለያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል። ዘገባው የኢዜአ እና የኢቢሲ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ምንጊዜም በላቀ የሥራ አፈጻጸም፣በላቀ ወታደራዊ ዲስፕሊን ሀገርና ሕዝባችሁን እንደምታገለግሉ እንተማመናለን” ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን
Next articleበፌዴራል ፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ-ካርታ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።