በአማራ ክልል የመጀመሪያው ሁሉን አካታች የአካል ጉዳተኞች አዳሪ ትምህርት ቤት ተገነባ።

101

ወልድያ ፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ)አመልድ ኢትዮጵያ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ሮቢት ከተማ ግንባታውን በ15 ሚሊዮን ብር ወጭ አከናውኗል። ሲቢኤም ኢጣሊ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለግንባታው የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ትምህርት ቤቱ 55 ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድም ተገልጧል።

የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ.ር) ግንባታውን ለማከናወን የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው ሲቢኤም ኢጣሊ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

አመልድ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን የገለጹት ዶክተር ዓለማየሁ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ወገኖች አመልድ ኢትዮጵያ ከረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በዘላቂነት እና በጊዜያዊነት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የራያ ቆቦ አሥተዳዳሪ ሞላ ደሱ አመልድ ኢትዮጵያ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ወገኖች ትኩረት ማድረጉ ለወረዳው በመልካም ተሞክሮነት የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡ አሥተዳደር ምክር ቤቱና ማኅበረሰቡ በመተባበር የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በማሟላት አዳሪ ትምህርት ቤቱ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አቶ ሞላ ተናግረዋል፡፡

የሲቢኤም ኢጣሊ ተወካይ አቶ ታዓምር ምስጋናው ድርጅቱ ለአካል ጉዳተኞች በጤና ፣ በትምህርት እና በሌሎች አስፈላጊ በሚባሉ ጉዳዩች ዙሪያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ አባል ወይዘሮ ሰውሀርግ ጌታቸው በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ሳይጨምር በክልሉ 4 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በመንግሥትም ኾነ በረጅ ድርጅቶች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ በመኾኑ በርካቶች የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጠቂ መኾናቸውን ወይዘሮ ሰውሀርግ አንስተዋል፡፡

አመልድ ኢትዮጵያ ከሲቢኤም ኢጣሊ ጋር በመተባበር ያከናወኑት ተግባር በሌሎች አካባቢዎች በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ያሉት ወይዘሮ ሰውሀርግ ለአካል ጉዳተኞች መንግሥትና ማኅበረሰቡ እንዲሁም ረጅ ድርጅቶች ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ባለ ዓለምየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ሰላማዊ በኾነ መንገድ መኾን እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ተናገሩ።
Next article“የሕዝብ ጥያቄዎች የአማራ ክልል አመራር የመታገያ ጥያቄዎች ናቸው” የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ