
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የጉለሌ ክፍለ ከተማ አማራ ተወላጆች የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ/ብአዴን/ኢሕዴን) 39ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብረዋል፡፡
በዕለቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የሕግ መምህር እና ተመራማሪ ሲሳይ መንገሥቴ (ዶክተር) የቀድሞ ኢህዴን-የአሁኑ አዴፓ ምሥረታ እና የትግል ጉዞን የሚያሳይና አሁን ላለችው ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን ያደረገውን አስተዋጽኦ የሚዳስስ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ አዴፓ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅት ሆኖ መመሥረቱ እና ታግሎ ሌሎችን ማታገሉ ለአሁኑ የውሕደት ውጤት እርሾ መሆኑንም ዶክተር ሲሳይ በጽሑፋቸው አመላክተዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አዴፓ ዋና ጸሐፊ አቶ ቻይና ሁሴን ‹‹የአማራ ተወላጆችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉንን አደረጃጃቶች ማጠናከርና በጋራ መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
በቅርቡ ይፋ ለሆነው የብልጽግና ፓርቲ እርሾ የሆነው የቀድሞው ኢሕዴን ይዞት የተነሳው ኅብረ ብሔራዊነት እና የኢትዮጵያዊ አንድነት እሳቤ መሆኑን ያነሱት የበዓሉ ታዳሚዎች ደግሞ ‹‹ሁሉም ይህን ጽናት ይዞ ሊቀጥል ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ መደራጀትና በአንድነት መቆም ወሳኝ ነው›› ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከነማ ፋርማሲዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ምሥጋን ከበደ ደግሞ አማራዉ መደራጀትና ለኢትዮጵያ አቅም መሆን እንዳለበት በመደራጀትም ሀገርን እንዲለውጥ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ