የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ሰላማዊ በኾነ መንገድ መኾን እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

95

ጎንደር ፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ መልዕክት በጎንደር ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሔድ የነበረው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተጠናቅቋል።

የከተማ፣ የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ አመራሮችን ባካተተው ኮንፈረንስ ከተሳተፉት መካከል አቶ አየነው ተገኝ ውይይቱ ነፃ እና ሀሳብን በግልጽ ለማስተላለፍ ያስቻለ ነበር ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ሰላማዊ በኾነ መንገድ ምላሽ ማግኘት የሚችልበት መንገድ ላይ መግባባት የተደረሰበት እንደነበር ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የአብሮነትና የመቻቻል ጥያቄ መሆኑን የጠቆሙት ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አይናዲስ አብዋ ናቸው።

እንደ ሕዝብ የገጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች በሦስቱ ቀን ውይይት መነሳታቸውንም አክለው ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አወቀ አስፈሬ በበኩላቸው አመራሩ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለመሥራት ቃል የገባበት ኮንፍረንስ መካሄዱንም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር ሊፈቱ ስለማይችሉ ለዚህም በባለቤትነት ከእህት ክልሎች ጋር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን በኮንፈረንሱ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

ውይይቱ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት ተጠናቅቋል።

ዘጋቢ- ምሥጋናው ከፍያለው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት 522 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል” የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ
Next articleበአማራ ክልል የመጀመሪያው ሁሉን አካታች የአካል ጉዳተኞች አዳሪ ትምህርት ቤት ተገነባ።