
ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዓመታዊ የአጋርነት የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ደመቀ ቦሩ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰተው ችግር 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈናቅለው በክልሉ ይገኛሉ። 11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት በከፍተኛ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጫና ውስጥ ይገኛል።
በክልሉ ሰባት ዞኖችና ሶስት ሜትሮፖሊታንት ከተሞችም በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እነዚህን ዞኖች መልሶ ለማቋቋም እና መልሶ ለመገንባት ደግሞ ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል።
ጉዳት የደረሰባቸውን ዞኖች መልሶ ለመገንባት ጥረት ቢደረግም የተገኘው ሀብት ዝቅተኛ በመኾኑ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን አንስተዋል።
መንግሥት ከሚያደርገው ሥራ ባለፈ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ የልማት ሥራዎች እና በመልሶ ግንታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች 374 ፕሮጀክቶች በክልሉ እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል። ድርጅቶች በቀጣይም የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዓለምነሽ ዋጋየ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ እያከናወኑ የሚገኙት የልማት ሥራ እና የሰብአዊ ድጋፍ የተለየ ዋጋ የሚሰጠው እንደኾነ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበት ክልል በመኾኑ በቀጣይ የሲቪል ድርጅቶች ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የማኅበረሰቡን ችግር በሚፈታ መንገድ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!