
ባሕርዳር : ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “በጎ ፈቃድ ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚተገበረውን ፕሮጀክት ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል የአምስት ዓመት ስምምነት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ባለሥልጣን እና ‘አሊያንስ ኬር ፎር ናው’ የተባለ አጋር ድርጅት ተፈራርመዋል።
በሁሉም ክልሎች የሚተገበረው ፕሮጀክት 5 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ነው። ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 5 ሚሊዮን ሀገር በቀል በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙ ተጠቁሟል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ተሰማርቷል።
በየጊዜው በተካሄዱ የማኅበረሰብ ንቅናቄዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በግለሰብ፣ በማኅበረሰብና በተቋም ደረጃ ባህል ሆኖ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ሰፊ አቅምን በመጠቀም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የተጎዱ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ፕሮጀክቱ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመደገፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ ያጠናክረዋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
ኢትዮጵያ መደጋገፍንና መተሳሰብን መሰረት ያደረጉ በርካታ ማህበራዊ እሴቶች ያሏት እንደመሆኗ ይህንን እሴት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብሮችን ከሌሎች ኢኒሼቲቮች ጋር በማስተሳሰር ለመተግበር ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉም በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አጋር ድርጅቶች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲኾን የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
በ2014 ዓ. ም የክረምት መርሐ-ግብር ከ24 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ መሳተፋቸው በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!