የሕዝቦችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን በብልጽግና ፓርቲ ኮንፈረንስ የተሳተፉ አመራሮች ተናገሩ።

46

ገንዳ ውኃ ፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን “ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ መልዕክት ለሦሥት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ኮንፈረንስ ተጠናቋል።

ኮንፈረንሱ በክልሉ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ዘርፈ ብዙ ችግርችን በጽናትና በቁርጠኝነት ለመታገል እና መተማመን ላይ ለመድረስ ያለመ እንደነበር የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ሳይፈቱ በመንከባለል ዘመናትን ያስቆጠሩ የአማራ ክልል ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች እንዲፈቱ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድም ሕዝቦች ጋር በጋራ ለመታገል እና ሕዝባዊ ኀላፊነትን በታማኝነት ለመወጣት ቁርጠኛ መኾናቸውን ነው ተሳታፊወቹ የገለጹት።

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው በኮንፈረንሱ አመራሩ የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነት እና መተማመን ላይ ተመርኩዞ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ለመታገል አቋም የተወሰደበት ነው ብለዋል።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እያሱ ይላቅ በክልሉ የሕግ የበላይነትን ማስፈን፣ በሕዝቦች የሚነሱ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን መፍታት፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፤ ፍትኃዊነትን እና የሕዝቦችን ሁለንተናዊ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ በኮንፈረሱ የጋራ መግባባት መደረሱን ገልጸዋል።

የሰላምና የጸጥታ ስጋቶችን በመለየት ሰላምና ልማትን በዘላቂነት ማረጋገጥ፤ በክልሉ ውስጥም ኾነ ከክልሉ ውጭ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞትና መፈናቀል ማስቆምና መታገል እንደሚገባም የጋራ አቋም መወሰዱንም ኀላፊው ጠቁመዋል።

የአመራር ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር እና ከሕዝቡ ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር የሕዝቡን ልማትና ሰላም ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባር እንደኾነ አቋም የተወሰደበት ኮንፈረንስ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ ናቸው።

ምዕራብ ጎንደር ዞን የክልሉን ሕዝብ መመገብ የሚችል ሰፊ የልማት ቀጠና መኾኑን ያነሱት አስተዳዳሪው በቀጣይ የዞኑን ሰላም በዘላቂነት በማስፈን የሕዝቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ነው ያነሱት።

ሰላምና ልማትን ያለሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደማይቻል የገለጹት አቶ ቢክስ በየደረጃው ያለ አመራር የዞኑን ሰላም እና ልማት ለማረጋገጥ ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ መታገል እንዳለበት ነው የተናገሩት። አመራሩ የትኛውንም መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲና በናቡ ፕሮጀክት ትብብር በምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ የተገነባ የጥቁር አዝሙድ ቅመም ማቀነባበሪያ ርክክብ ተደረገ።
Next articleወላጆቻቸውን ያጡና በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ኾነ