
ጎንደር፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቁር አዝሙድን እሴት በመጨመር ለማቅረብ የሚያስችል የማቀነባበር ሥራ በምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ 51 ለሚደርሱ አርሶ አደሮች ግንባታው ተጠናቆ ርክክብ ተደርጓል ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኙት ምሥራቅና ምዕራብ ደንቢያ እንዲሁም አለፋና ጣቁሳ ወረዳዎች በጥቁር አዝሙድ ምርትና በሌሎች ቅመማ ቅመሞች ምርት ይታወቃሉ።
በወረዳዎቹ ምርቱን በጥሬው ከመሸጥ ያለፈ ሥራ እንዳልነበረበትም ይታወቃል።
በመኾኑም ጎንደር ዩኒቨርሲቲና ናቡ ፕሮጀክት በጋራ በመኾን ከ700 ሺ ብር በላይ በኾነ ወጪ የጥቁር አዝሙድ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በማኅበር ለተደራጁ አርሶ አደሮች ድጋፍ አድርገዋል።
በርክክብ ወቅቱ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) የጥቁር አዝሙድ ዘይትን እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ለማቅረብ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ጎንደር ዩኒቨርሲቲና ናቡ ፕሮጀክት የጥቁር አዝሙድ ማቀነባበሪያ ከመክፈት በተጨማሪ የጥቁር አዝሙድ ምርትን ማሳደግ ላይ ይሠራሉ ተብሏል።
እንዲሁም በጣናና አካባቢው የሚከሰቱ አረሞችን የማጥፋት ሥራ ይሠራል።
የጥቁር አዝሙድ ዘይት በአካባቢው ላይ ያለው ተፈላጊነት በጥናት ተደግፎ መጀመሩም ተገልጿል።
አርሶ አደሮቹ ጎንደር ዩኒቨርሲቲና ናቡ ፕሮጀክት ባደረጉላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው እስካሁን ከነበረው ጠቀሜታ የተሻለ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
የጥቁር አዝሙድ መጭመቂያ ፋብሪካው በቀን 15 ኩንታል ጥቁር አዝሙድ የመጭመቅ አቅም እንዳለውና ከአንድ ኩንታል ጥቁር አዝሙድ 25 ሊትር ዘይት ይገኘዋልም ተብሏል።
አንድ ኩንታል እየተሸጠበት ካለው ወደ ዘይት ሲቀየር የ8ሺ ብር ልዩነት እንዳለውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!