
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ድርጅቶቹ በክልሉ የሠሯቸውንና በሂደት ላይ ያሉትን ሥራዎች የሚያሳይ ኤግዚቪሽን ተዘጋጅቷል።
በአማራ ክልል ከ160 በላይ ሀገር በቀልና የውጭ ድርጅቶች በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት፣ በሥራ እድል ፈጠራና በአደጋ ጊዜ ምላሽ መሥጠት ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛል።
ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ደግሞ ወርልድ ቪዥን አንዱ ነው። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በላይ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የወርልድ ቪዥን ሰሜን ምስራቅ አስተባባሪ ሞልቤቶ ታደሰ ነግረውናል።
ድርጅቱ ከዚህ በፊት በውሃ፣ በምግብ ዋስትና በህጻናት ጥበቃና እንክብካቤ፣ በጤና እና በትምህርት የልማት ሥራዎች ላይ ሲሠራ መቆየቱን ነው የገለጹት።
ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው ስምንት ዞኖች በሚገኙ 11 ወረዳዎች መልሶ ማቋቋምና የአደጋ ምላሽ መሥጠት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚህም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ፈንድ በማፈላለግ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።
የ”ሄልቬታስ ኢትዮጵያ” አማራ ክልል የተንጠልጣይ ፕሮጀክት ማናጀር ተስፋሁን ሞላ እንዳሉት ደግሞ ድርጅቱ ከ30 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። በአማራ ክልልም በግብርና፣ በአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በመልካም አስተዳደር፣ የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ፣ በመጠጥ ውኃና መሰል ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ከልማት ሥራዎች ባለፈ በክልሉ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን በመጠገን፣ የግብርና ግብዓት በማቅረብና ሰብአዊ ድጋፍ ላይ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የ “ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዲቨሎፕመንት” ሪጅናል ማናጀር አልማዝ መኮንን ፤ በክልሉ ከልማት ሥራዎች በተጨማሪ አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች በጦርነቱ ጉዳት በደረሰበቸው አካባቢዎች በ14 ሚሊዮን ብር ወጭ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ድርጅቶቹ በቀጣይም ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የልማት ሥራዎች ከማከናወን ባለፈ ማኅበረሰቡን መልሶ የማቋቋም ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የተዘጋጀው ኢግዚቪሽን ድርጅቶች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና በጋራ አብሮ እንዲሰሩ አቅም እንደሚፈጥር አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!