በአማራ ክልል ባለፉት 10 ወራት 30 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

46

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው የገቢ ግብር በ10 ወራት ውስጥ 30 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የክልሉን የሰላም እና የልማት እቅዶችን ለማሳካት 42 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህንን እቅድ ለማሳካት ባለፉት 10 ወራት በተሠሩ ሥራዎች 30 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አግማስ ጫኔ ተናግረዋል፡፡ ይህም ከእቅዱ 75 ነጥብ 15 በመቶ መከናወኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወይም 41 በመቶ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

የተሻለ አፈጻጸም ከታየባቸው ዋና ዋና የገቢ አርእስቶች መካከል ከግል ድርጅት ተቀጣሪ ሠራተኞች የተሰበሰበው ግብር 92 በመቶ ሲኾን ከኪራይ ግብር 75 በመቶ መሰብሰቡን አቶ አግማስ ተናግረዋል ፡፡

መካከለኛ አፈጻጸም ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል ከንግዱ ማኀበረሰብ የንግድ ትርፍ ገቢ 71 በመቶ የተሰበሰበ ሲኾን ከተጨማሪ እሴት ታክስ 70 በመቶ ግብር በ10 ወሩ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ቀጥተኛ ካልኾነ ታክስ፣ የእርሻ ሥራ ገቢ ግብር እና የመሬት መጠቀሚያ ገቢ 40 በመቶ በመሰብሰቡ ዝቅተኛ አፈጻጸም ተመዝግቦበታል ብለዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ ከተሞች መካከል በ10 ወሩ አበረታች ገቢ ከሰበሰቡ መካከል ወልዲያ እና ደብረታቦር ከተሞች ተጠቃሽ መኾናቸውን አቶ አግማስ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ሁለቱ ከተሞች የእቅዱን 97 በመቶ ፈጽመዋል፡፡ በዞን ደረጃ ዋግ ህምራ 92 በመቶ በመፈጸም የተሻለ አፈጻጸም አለው ብለዋል፡፡

ዝቅተኛ አፈጻጸም ከነበራቸው ከተሞች መካከል ደሴ 56 ነጥብ 6 በመቶ ፣ ኮምቦልቻ 65 በመቶ ፣ ጎንደር 68 በመቶ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡

ለዝቅተኛ አፈጻጸሙ መንስኤዎች መካከል ቀጥተኛ ያልኾነ ታክስ የኀብረተሰቡን ተሳትፎ እና የንግዱን ማኀበረሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመኾኑ ደረሰኝ የመቁረጥ ልምድ በሚፈለገው ደረጃ አለመዳበር እንደ ምክንያት ተቀምጧል፡፡ የእርሻ ሥራ ገቢ ግብር እና የመሬት መጠቀሚያ ገቢ አዋጅ ይለወጣል በሚል ሥራው ዘግይቶ መጀመሩ ሌላው በምክንያትነት መኾኑ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በየአካባቢው የተፈጠረው የሰላም እጦት ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መኾን ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

ግብር ለኀብረተሰቡ ሁሉ ነገር ነው ያሉት አቶ አግማስ ግብር ከሌለ የልማት እና የሰላም ሥራዎችን ማከናወን እና የኀብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች መመለስ ስለማይቻል አመራሮች ገቢ በመሰብሰብ በኩል በቁርጠኝነት እንዲሠሩ አሳስበዋል ፡፡

የግብር ገቢ በመሰብሰብ ረገድ የኀብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን ያነሱት አቶ አግማስ፤ ኅብረተሰቡ የግብር መሰወር እና ማጭበርበር ወንጀሎችን፣ አየር በአየር ንግዶችን በማጋለጥ እና በመጠቆም እንዲሁም ደረሰኝ በመቀበል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ገቢ በመሰብሰብ በኩል የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ገቢ በመሰብሰብ በኩል ድርሻቸውን በአግባቡ በመፈጸም እንዲተባበሩ አሳስበዋል፡፡ በቀጣይ ከገቢ ተቋሙ በኩል ቀሪውን 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ከዚህ በፊት ከተደረገው ጥረት በተሻለ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ፋሲካ ዘለዓለም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጤፍና ከጤፍ የሚዘጋጁ ምግቦችን የማስተዋወቅ ፕሮግራም በሮም የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ግቢ ተካሔደ።
Next articleየብልፅግና ፓርቲ 10 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው።