
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የእህል ዘሮች ቀን በማስመልከት የኢትዮጵያን የጤፍ ምርትና ከጤፍ የሚዘጋጁ ምግቦችን የማስተዋወቅ ፕሮግራም ሮም በሚገኘው የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት(FAO) ዋና መሥሪያ ቤት ተካሄዷል።
የግብርና ሚኒስቴር እና በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር በተዘጋጀው መርሐ-ግብር ላይ ተቀማጭነታቸውን ሮም ያደረጉና በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ሰራተኞች፣ ሮም የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች እና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ ኢትዮጵያ የዘርፈ ብዙ ባህል፣ ሃይማኖትና ወግ ባለቤት የሆኑ ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗን አውስተዋል።
በኢትዮጵያ ተወዳጅ የሆኑ የምግብ ዓይነቶች እንዳሉና ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው የሚመገቡት ምግብ ከጤፍ የሚዘጋጀው እንጀራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ጤፍ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለሺህ ዓመታት ሲያመርቱት የቆየ እንዲሁም የሀገሪቷ ሀገር በቀል የእህል (ሚሌት) ዝርያ እና መለያ በመሆኑ “አንድ አዝዕርት በአንድ ሀገር” በሚለው የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ፕሮግራም ኢትዮጵያ ጤፍን መርጣ እየሰራችበት መሆኑ ተጠቁሟል።
በማስተዋወቂያ መርሐ-ግብሩ ላይ ከኢትዮጵያ ምግቦች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃና ዳንስ፣ቡና እና ሌሎች የባህል መገለጫዎች ለታዳሚዎቹ መቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!