ክልሎች በመጋዘን የሚገኘውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶአደሩ በወቅቱ እንዲያደርሱ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

140

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሎች በመጋዘን የሚገኘው ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶአደሩ በወቅቱ ማድረስ እንደሚገባ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።
ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ22ኛ መደበኛ ስብሰባው የግብርና ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የ 10 ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ገምግሟል።

በወቅቱ የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት፤ ለ2015/16 ምርት ዘመን 12 ነጥብ 87 ሚሊዮን ኩንታል በመግዛት እና የከረመውን ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ጨምሮ በምርት ዘመኑ በአጠቃላይ 15 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ይቀርባል።

ወደአገር ውስጥ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የደረሰው ከ50 በመቶ የማይበልጥ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በየክልሎች እየታየ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት በማሻሻል ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ እና የአፈር ማዳበሪያን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ሂደት ላይ ማሻሻያ በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት የአፈር ማዳበሪያን በታህሳስ ወር ከመጫን ይልቅ ቀደም ብሎ ሐምሌ ወር አካባቢ መጫን እንዲቻል አሰራሩን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያን ካሳ በበኩላቸው፤ በክትትል ወቅት ከክልሎች በተሰበሰበ መረጃ መሰረት እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ብቻ ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።

ቀሪው አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በማዕከላዊ መጋዘን እና በህብረት ሥራ መጋዘኖች ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከክልሎች ጀምሮ እስከ ቀበሌዎች ድረስ ያሉት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ኃላፊነት በመውሰድ ያላቸውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲያደርሱ አሳስበዋል።

ከፍተኛ የማዳበሪያ ተጠቃሚ ከሆኑት ክልሎች ለኦሮሚያ ክልል ሶስት ሚሊዮን ኩንታል እንዲሁም ለአማራ ክልል አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ የተላከ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።

የከረመ ማዳበሪያ ጋር በድምሩ ኦሮሚያ አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል፤ አማራ ክልል ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በመጋዘን የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ተጨማሪ መጠን የአፈር ማዳበሪያ ወደየክልሎች የሚጓጓዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ በየዞኖቹ እና ወረዳዎቹ እስካሁን የደረሳቸው የአፈር ማዳበሪያ ከተቀመጠላቸው ኮታ ያነሰ መሆኑንም አንስተዋል።

እንድ ኢፕድ ዘገባ፣ ለሁሉም ክልሎች የሚደረገው የአፈር ማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ስርጭት ካልተጠናቀቀ አርሶ አደሩ ያለአፈር ማዳበሪያ ለመዝራት የሚገደድ በመሆኑ የማዳበሪያ ስርጭቱ በወቅቱ መጠናቀቅ እንደሚገባው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ሊሻሻል እና ወደ ክልሎች የተሰራጨው ማዳበሪያም ለአርሶ አደሩ መድረሱ ላይ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የማጣራት ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ በመታገዝ የ21ኛ ክፍለዘመን የሚጠይቀውን የግብርና ምርት ላይ መድረስ ይገባል” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Next articleጤፍና ከጤፍ የሚዘጋጁ ምግቦችን የማስተዋወቅ ፕሮግራም በሮም የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ግቢ ተካሔደ።