
ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ፕሬዚዳንቷ ለአንድ ወር የሚቆየውን ሳይንስ ሙዚየም አውደ ርእይ ጎብኝተዋል።
አውደ ርእዩ የሁሉም ክልሎች ቀን የተሰየመለት ሲኾን ዛሬ ደግሞ የደቡብ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ቀን ነው።
በዚህ እለት በሙዚየሙ ተገኝተው የጎበኙት ርእሰ ብሔሯ በርካታ የሕዝብ ቁጥር የያዘውን ግብርና ለማዘመን የተደረጉ ጥረቶችን ተመልክቻለሁ ብለዋል። ፕሬዚዳንቷ በግብርናው ዘርፍ ፈጠራ እየተበረታታ መምጣቱን በማየቴ ደስ ብሎኛል ብለዋል።
በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ካልታገዝን 21ኛውን ክፍለዘመን መቀላቀል አንችልም ያሉት ርእሰ ብሔሯ ለዚህ ደግሞ ጅመሮችን በአውደ ርእዩ ተመልክቻለሁ፤ ይህንን የሀገር አቅም በማስተባበር የወጣቶችን ጉልበት እና ዕውቀት አጣጥሞ በመጠቀም ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ መድረስ ይገባናል ብለዋል።
ዛሬ በሳይንስ ሙዚም የተመለከትኩት የደቡብ ክልል ማሳያም ሀገራችን ወደፊት በግብርናው ዘርፍ ብዙ ተስፋ እንዳላት ያመላከተም ነበር ብለዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የደቡብ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊው ኡስማን ሱሩር አውደ ርእዩ የግብርና አምራቹን ከግብአት አቅራቢው እና ተመራማሪ ጋር ያገናኘ መኾኑን ገልጸዋል። እንደ ክልል ልምድ አካፍለናል እኛም ልምድ ወስደናል ብለዋል ኀላፊው።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!