ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚያስፈልገው የደቅ ደሴት ወደብ ግንባታ ዛሬ መጀመሩን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

59

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ጸጋ ከተሰጣቸው የጣና ሐይቅ ገጸ በረከቶች መካከል የደቅ ደሴት አንዷ ነች፡፡ ሙሉ በሙሉ በውኃ ለተከበበችው ደቅ ደሴት ብቸኛው የትራንፖርት አማራጭ የባህር ላይ ትራንስፖርት ነው፡፡

የወደቡ ግንባታ በደቅ ደሴት ውስጥ ከሚገኙት ገዳማት አንዷ የኾነችውን እና በ1337 ዓ.ም እንደተመሠረተች ለሚነገርላት ቀደምቷ ፈለገ ሕይዎት ጣና ሐይቅ ቅድስት አርሴማ ገዳምን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በተንጣለለው የጣና ሐይቅ ውስጥ ከከተሙት በርካታ ደሴቶች መካከል አንዷ የኾነችው ደቅ ደሴት ስምንት የሚደርሱ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናትን አቅፋ ይዛለች፡፡ ከበርበሬ እስከ ፍራፍሬ እያመረተች ለባሕር ዳር ከተማ ገበያ በማቅረብ የምትታወቀው ደቅ በአቅራቢያዋ ወደብ አለመኖሩ ለዘመናት ችግር እንደ ነበር ነዋሪዎቹ አንስተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ “ፈረንጅ ቡስኪን” ይሉታል፤ ደቅ ላይ የጣሊያን መንግሥት ወደብ ለመሥራት ያስቀመጠው ታፔላ ወይም የማስታወቂያ ሰሌዳ ዛሬም ድረስ አልተነቀለም። ወደቡም አልተገነባም ነበር፡፡ የወደቡ ግንባታ ትርፍ አምራች ለኾነችው የደቅ ደሴት በተለይም ቀደምት እና ታሪካዊ ለኾነችው ፈለገ ሕይዎት ጣና ሐይቅ ቅድስት አርሴማ ገዳም የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያስፈልግ ነበር ያሉት የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኅላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ በቅርብ ዓመታት ወደቡን ለመሥራት የተደረገው ሙከራ በተለያዩ ችግሮች ሳይሳካ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ለደሴቷ ነዋሪዎች እና ለገዳሟ ጎብኝዎች ወደብ እንደሚያስፈልጋቸው በማመኑ ለክልሉ መንግሥት ያቀረበው የበጀት ጥያቄ ይሁንታ አግኝቶ ዛሬ የግንባታ ሥራው ለማስጀመር ተችሏል ያሉት ኅላፊው ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ 13 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልገዋል፤ ነገር ግን ለጊዜው 12 ሚሊዮን ብር ተፈቅዶ ሥራው ዛሬ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ሥራውን በተያዘለት መርኃ ግብር ለማጠናቀቅ የሕዝቡ ቀና ተሳትፎ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጣሂር የወደብ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መሥጠት ሲጀምር ከጎርጎራ ናርጋ የሚመጡ ጎብኝዎች ቀደምቷን የቅድስት አርሴማ ገዳም ለመጎብኘት ዕድል ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

የደቅ ደሴት የወደብ ግንባታ የተጠናው በጣሊያን ወረራ ዘመን ነበር ያሉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ እንዳለው ፈንታው ለብዙ ዘመናት ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ሳናገኝ ቆይተናል ብለዋል፡፡ የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም የዘመናት ጥያቄያችን መመለሱ ተገቢ እና የአካባቢውን ጸጋ ወደ ከተማ ማድረስ እጅግ አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቀደምት ከሚባሉት የቅድስት አርሴማ ገዳማት መካከል ቀደምት የኾነችው እና በ1337 ዓ.ም የተመሠረተችው ፈለገ ሕይዎት ጣና ሐይቅ ቅድስት አርሴማ ገዳም ናት የሚሉት ነዋሪው ወደ ገዳሟ የሚመጡ ጎብኝዎችን እና ምዕመናንን ወደቡ ያለስጋት ለማድረስ ይረዳል ብለዋል፡፡ የወደቡ ግንባታ የደሴቷ ማኀበረሰብ የቆየ ጥያቄ በመኾኑ በተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ለሕዝብ ውይይት በማድረግ አካባቢያዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ።
Next article“በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ በመታገዝ የ21ኛ ክፍለዘመን የሚጠይቀውን የግብርና ምርት ላይ መድረስ ይገባል” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ