የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት በማድረግ አካባቢያዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ።

57

ባሕርዳር : ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሮ ዲቨሎፕመንት ኔትወርክ ድርጅት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ ወረዳዎች ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን ለመፍታት ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የሚሠራ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ በጅሌ ጥሙጋ ፣ ኤፍራታ እና ግድም፣ አጣየ እና ሰንበቴ ከተሞች ላይ የግጭት መሠረታዊ ምክንያቶችን በማጥናት መፍትሔ ለማፈላለግ እንደሚሠራ ከአጋር አካላት ጋር ባደረገው ውይይት አስታውቋል።

የፕሮ ዲቨሎፕመንት ኔትወርክ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አህመድ ሁሴን ድርጅታቸው በአጣዬ እና በሰንበቴ ከተማዎች ሠላም ርቆት የቆየ ቢኾንም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል በተደረገ ውይይት ነዋሪዎቹ በጸብ ከመፈላለግ ወጥተው በሠላማቸው ላይ እንዲመክሩ እያደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ግጭት ሰዎችን ለሞት፣ ንብረትን ለውድመት የሚዳርግ ማኀበራዊ ቀውስ ነው ያሉት አቶ አህመድ ግጭት ቀስቃሽ አካላት እሳቱ የማያቃጥላቸው፣ የሕዝቡ መፈናቀል፣ ለርሃብ መዳረግ የማይገዳቸው እሳቱን ከዳር ቆመው የሚሞቁ መኾናቸውን ከሕዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ውይይት ማድረግ የችግሩን 50 በመቶ እንደመቅረፍ ይታሰባል የሚሉት አቶ አህመድ ፕሮ ዴቨሎፕመንት ኔትወርክ እየሠራ ባለው ተግባር በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን እና በቀጣይም የተጠናከረ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ያለበት ውይይት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) በክልሉ በርካታ ሰው ሠራሽ ግጭቶች መከሰታቸውን አስታውሰው በተለይ በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሚያ ብሔረሰብ አሥተዳደር አጎራባች አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ችግሮች የተጀመሩ መልሶ ግንባታዎች መቋረጣቸውን ጠቁመዋል።

ሰላም ቅድሚያ የሚሠጠው ጉዳይ መኾኑን ያነሱት ዶክተር አባተ የአማራ ክልል የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ መቋቋም እና ልማት ፈንድ ችግሩን ለመፍታት ያገባኛል የሚሉ አካላት ተሰባስበው ለአንድ ዓላማ የሚቆሙበት መንገድ እየተመቻቸ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ደህንነት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ በአጎራባች አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

የችግሩ ተጠቂ ማኅበረሰቡ ይሁን እንጅ የችግሩ ባለቤት ወይም ጥቅም ፈላጊዎች ሕገ ወጥ መሳሪያ አዘዋዋሪዎች፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተሿሚዎች መኾናቸውን በነበረው ውይይት ማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል።

ማኅበረሰቡ ያልታሰቡ ግጭቶች ሲፈጠሩ ጸቡን ከማባባስ ወጥቶ ማን አለ? መቼ?የት? የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ የችግሩን ምንጭ መለየት አለበት ብለዋል።

የክልሉ የጸጥታ አካላት መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች እና ከሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር ተባብረው እየሠሩ በመኾናቸው ውጤት አምጥቷል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልሉ መንግሥት ማልማት ለሚችሉ እውነተኛ እና ቁርጠኛ ለኾኑ ባለሐብቶች አስፈላጊውን መሬት የሚያቀርብ መኾኑን አረጋግጣለሁ።” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚያስፈልገው የደቅ ደሴት ወደብ ግንባታ ዛሬ መጀመሩን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡