
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ አስተዳደር እና በአዋሳኝ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደነበሩ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ ግጭቶቹን በዘላቂነት ለመፍታትም ዛሬ ከሁለቱም ብሔሮች የተውጣጡ ሰዎች በተገኙበት እርቀ ሠላም እየወረደ ነው፡፡
በአጣየ ስታዲዬም እየተካሄደ ባለው የእርቅ ሥነ ስርዓት ከሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ እና ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች ከሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደግሞ ጂሌ ጥሙጋ ወረዳ 24 ቀበሌዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ታየ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያንም የሚበቃ ፀጋ እንዳላቸው በመግለጽ ፀጋውን በጋራ ለመጠቀም መፋቀርና መተሳሰብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹አብሮነታችንን፣ ሠላማችንን ለማደፍረስ እና ለማጥፋት የሚሠሩ አሜኬላዎችን መንቀል ያስፈልጋል›› ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሐሰን ደግሞ የእርቅ ሥነ ስርዓቱ ያለምክንያት ሕይወት እና ንብረት የጠፋበት ጊዜ የሚወቀስበት መሆኑን ገልጸው ‹‹ቀጣዩ ጊዜ ወደተሻለ የምንጓዝበት፣ ለልጆቻችን የተሻለ ነገር እና አካባቢ የምናቆይበት መሆን አለበት›› ብለዋል።
ነዋሪዎቹም እስካሁን የተደረጉ ግጭቶች ምክንያታቸው ያልታወቁ መሆናቸውን ገልጸው የሁለቱን ሕዝቦች የዘመናት አብሮነት የናደ መኑን ተናግረዋል። አካባቢው የሁለቱን ሕዝቦች አብሮነትና ሠላም የሚንዱ ሰዎች መደበቂያ እንዳልሆነ በጋራ ሠላማቸውን ለማስጠበቅ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በእርቅ ሠላም ሥነ ስርዓቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ይርጉ ፋንታ -ከአጣዬ