“የክልሉ መንግሥት ማልማት ለሚችሉ እውነተኛ እና ቁርጠኛ ለኾኑ ባለሐብቶች አስፈላጊውን መሬት የሚያቀርብ መኾኑን አረጋግጣለሁ።” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

58

ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በዛሬው እለት አርዲ እምነበረድና ቀለም ፋብሪካን ተመልክተዋል። ፋብሪካው በግንባታው ዘርፍ ያለውን የግብአት ጉድለት በመሙላት ረገድ ጉልህ ድርሻ ማበርከት የሚችል ነው ብለዋል።

በሀገራችን የልማት መስፋፋት ትልቁ ማነቆ ካፒታል ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል በዚህም ምክንያት አቅም ያለው ባለሐብትና የቴክኖሎጂ አቅማችን በጣም ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

አርዲ እምነበረድና ቀለም ፋብሪካ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሙሉ አቅም ለማምረት መብቃቱ ትልቅ እድገት ነው። በበርካታ ጉዳይ ጥገኛ የነበረውን ኢኮኖሚያችን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንደምንችል ማሳያ ጭምር ነው ብለዋል።

አማራ ክልል በማዕድን ሐብት ታዋቂ አልነበረም። ነገር ግን ከክልላችን አልፎ ሀገሪቱን ሊለውጥ የሚችል የማዕድን ሐብት አለን። ይሔንን በመረዳት ባለሐብቶች በተለያዩ ዘርፍ ተሰማርቶ ማልማት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ ነው። ዘርፋን ለማልማት የሚመጡ አቅም ያላቸው ባለሐብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተው ወደሥራ እንዲገቡ እናደርጋለን ብለዋል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ቦታ ወስዳችሁ በተፈለገው ጊዜ ወደስራ ያልገባችሁ ባለሐብቶች ግንባታዎቻችሁን አጠናቅቃችሁ ወደምርት እንድትገቡ ጥሪየን አስተላልፋለሁ ብለዋል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት።

መሬት የምንሰጠው ፋብሪካ ተጠናቅቆ ምርት እንዲመረትበት፣ የሥራ እድል እንዲፈጠርበት በመኾኑ የክልሉ መንግሥት ማልማት ለሚችሉ እውነተኛ እና ቁርጠኛ ለኾኑ ባለሐብቶች አስፈላጊውን መሬት የሚያቀርብ መሆኑን አረጋግጣለሁ ብለዋል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮ ቴሌኮም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያቋቋሙት ስማርት የመማሪያ ክፍል በዛሬው እለት ሥራ ጀመረ።
Next articleየሕዝብ ለሕዝብ ውይይት በማድረግ አካባቢያዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ።