“አማራ ክልል ሀገሪቱን ሊለውጥ የሚችል የማዕድን ሃብት ያለው መኾኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው” የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

106

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር) በባሕር ዳር ከተማ በ687 ሚሊዮን ብር የተገነባውን
አርዲ ፣ቀለምና እምነበረድ ማእድን መፍጫና ማሸጊያ ፋብሪካ የሙከራ ምርት እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።

በምልከታው በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)፣ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ፋብሪካው ለ298 ሰዎች የሥራ እድል የፈጠረ ነው።

የአርዲ ማኑፋክቸሪንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዷለም የሺዋስ እንዳሉት የኢንቨስትመንት መሬት በተሰጣቸው ማግስት በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ በመግባት በአሁኑ ወቅት ተመጋጋቢ የሆኑትን እብነ በረድ፣ ቀለምና የካልሺየም መፍጫና ማሸጊያዎችን በሙከራነት እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ለፕሮጀክታቸው የተሰጣቸው መሬት ጠባብ በመሆኑ የማስፋፊያ ቦታ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ታምራት ደምሴ የማዕድን ዘርፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል 40 የሚደርሱ ማዕድናት መኖራቸውን ያነሱት አቶ ታምራት ለሥራ እድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋጾ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ባሕር ዳር የኢንቨስትመንት ማዕከልነቷ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል። አርዲ ቀለምና እምነበረድ ማእድን መፍጫና ማሸጊያ ፋብሪካ ችግሮችን ተቋቁሞ ግንባታውን በማፋጠን ወደ ሙከራ ምርት መግባቱ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

አማራ ክልል አገሪቱን ሊለውጥ የሚችል የማዕድን ሐብት ያለው መሆኑን እያረጋገጠ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ
ያሉ ጸጋዎችን በሙሉ አቅም እየተጠቀሙ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ማርካት ይጠይቀናል ብለዋል።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሐብቶች ለሥራ እድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸውም ነው ርእሰ መስተዳድሩ ያረጋገጡት።

መንግስት ባለሃብቶችን ለማገዝ ቁርጠኛ አቋም አለው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ወደ ስራ ያልገቡ ባለሐብቶች ችግሮችን በመቋቋም ወደ ሥራ ገብተው የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የተሰጣቸውን የኢንቨስትመንት ቦታ በአግባቡ ተጠቅመው ተጨማሪ የማስፋፊያ መሬት ለሚጠይቁ ባለሃብቶች መንግስት ቀልጣፋ ምላሽ እንደሚሰጣቸውም አረጋግጠዋል።

የህግ የበላይነትን እያረጋገጥን የማዕድን ሐብታችንን ጨምሮ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ውጤታማ ተግባራትን እያከናወን እንቀጥላለን ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።

ዘጋቢ፦ ስማቸው እሸቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጉዛራ ቤተ-መንግስት የጥገና ሥራ ተጀመረ።
Next articleየኢንዱስትሪ ሚኒስተሩ አቶ መላኩ አለበል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውን የፋሽን ኤግዚቢሽንና ባዛር ጎበኙ።