ጎንደር አሁንም ስለሠላም ጥሞና ላይ ናት፡፡

228

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ የእስልምና ሃይማኖት ዑለማ ምክር ቤት ለአንድ ወር የታወጀው ፀሎት እንደቀጠለ ነው፡፡ ወጣቶች ሠላምን ለማምጣት በባለቤትነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱና የትልልቅ ሰዎችን ምክር ሊሰሙ እንደሚገባም ተነግሯል፡፡

የጃሚዐል ከቢር መስጂድ ጎንደር ከተማ ላይ ትልቁ መስጂድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በከተማው የእስልምና ሃይማኖት የዑለማ ምክር ቤት ለ30 ቀናት የሚዘልቅ ስለ ኢትዮጵያ ሠላም ጸሎት የሚደረግበት ‹ቁኑት› የተባለ የጸሎት ሥነ ስርዓት አውጇል፤ ሥነ ስርዓቱን ተከታትለናል፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸው አማኞች በመስጂዱ በየቀኑ ይታደማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሁሉ ሠላም እንዲሰፍንና የሰው ልጆች ደኅንነት እንዲረጋገጥ አሏህ የሚስተዋለውን ሰፊ የፀጥታ ችግር እንዲያስወግድ ተንበርክከው ይማጸናሉ፡፡

አህመድ አብደላ በጸሎት ሥነ ስርዓቱ ያገኘሁት ወጣት ነው፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ያለውን የእርስበርስ ግጭት አሏህ እንዲያበርደው በማሰብ ሕዝበ ሙስሊሙ ሁሉ ጸሎት እያደረገ ነው፤ እኔም የድርሻዬን ስለሠላም አምላኬን እየተማጸንኩ ነው›› ብሏል፡፡

ሌላኛው ሐሳብ የሰጠን ሷሊህ ታጁ ደግሞ የጸሎት ሥነ ስርዓቱ በዑለማዎች የታዘዘ ‹ቁኑት› የተሰኘ ጸሎት እንደሆነ ጠቅሶ ‹‹ሀገር አንዳች ችግር ሲያጋጥማት ማለትም የጦርነት፣ የርሃብ፣ የዝናብ መጥፋት ወይም የዝናብ መብዛትና መሰል ትልልቅ ችግሮች ሲፈጠር ሙስሊሙንም ሆነ ክርስቲያኑን የሚጎዳ ችግር ሲመጣ የሚታወጅ ጸሎቱ ነው፡፡ ሁሉን ነገር አብርደው፤ ሠላሙን ስጠን ማለት ነው›› ብሏል፡፡

ሀጂ አሊ መሐመድ በጎንደር ከተማ ውስጥ አሉ ከተባሉ ዑለማዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋር በነበረን ቆይታ ደግሞ ‹‹በኢትዮጵያ በተለያዬ ግርግር የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ሰው እየተራራቀ፣ እየተጣላ በትርምስ እንደልብ ወጥቶ መግባት የማይቻል ሲሆን ጌታ እንዲያረጋጋው እንዲህ ተሰብስበን ጸሎት እናደርጋለን፤ ሰሞኑንም አምስት ጊዜ በምንሰግደው ስግደት እንዲታሰብ ለአንድ ወር አውጀናል፡፡ መጨረሻ ላይ ደግሞ በዱዐ ቁኑት ዱዐ ሊቀራ በየመስጅዱ አዝዘናል›› ብለውናል፡፡

አህመድ አብደላ ‹‹በተለይ ወጣቱ የትልልቆችን የሃይማኖት አባቶች ምክር መስማት አለበት፣ በተለያዬ መልክ ከሚሰበከው ዘረኝነት እራሱን ሊያርቅ ይገባል፣ ነቢያችን በግልፅ ‹ዘረኝነት ጥንብ ናት› ብለው ተናግረዋል፡፡ ሰው ሁሉ እንደ ማበጠሪያ ጥርስ እኩል ነው፡፡ ስለዚህ በምንም መልኩ ሠላምን ለማምጣት እራሳችንን ከዘረኝነት ማጽዳት አለብን›› ብሏል፡፡

ሷሊህ ታጁ ደግሞ ‹‹እያንዳንዱ ሰው ሠላምን ለማምጣት እኔም ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ማሰብ ይገባዋል፡፡ ሁሉም ሰው በሚችለው መጠን ሠላምን ከሚያርቁ ነገሮች እራሱን ማራቅ ይኖርበታል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ስለምንጽፈው እና ስለምናሰራጨው ሐሳብ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ሁሉም ስለሠላም መምጣት ከተጨነቀ ሠላም ይመጣል›› የሚል ምክረ ሐሳቡን ሰጥቷል፡፡

ሀጂ አሊ ደግሞ ‹‹ሃይማኖታችን ከማንም በላይ የሚያስተምረን ሠላምን ነው፡፡ ያንን በማሰብ መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ የሰው ልጅ ቀርቶ እርጥብ ዛፍ እንኳን ‹ፈጣሪን ስለሚያመሠግን አይቆረጥ› ነው የሚባለው፡፡ ውሻ ቱታ እየለበሰ ገላውን እየታጠበ ሶፋ ላይ እንዲተኛ እየተደረገ ባለበት ዘመን የሰው ልጅ እንደ ቅጠል እየረገፈ ትርምስ ላይ መግባት አልነበረበትም፡፡ መስማማት እንኳን ቢያቅት በመቻቻል ሀገርን መጠበቅ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ሠላምን ለማምጣት በጎንደር እንደሚታየው በሃይማኖት ተቋማት አማኞችን የማስተማር ሥራው በሁሉም ቦታ ተጠናክሮ ቢቀጥል፤ ሕዝብ የአዕምሮ ሠላም የሚያገኝ አዕምሮ ሠላም ሲሆን ደግሞ ሐሳብም ሠላም ይሆናል፡፡ ሐሳብ ሠላም ከሆነ ድርጊት የሐሳብ ውጤት ነውና ሠላማዊ ይሆናል፤ መልካም ቀን፡፡

ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ -ከጎንደር

Previous articleበአጣየ ከተማ የእርቀ ሠላም ሥነ ስርዓት እየተካሄደ ነው፡፡
Next articleበአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሉም ክፍለ ከተሞች አዴፓ 39ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡