
አዲስ አበባ ፡ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት የአሚኮ አዲስ አበባ ስቱዲዮን አጠቃላይ ሥራ እና የአዲሱን ስቱዲዮ የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው አሚኮ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቋንቋዎች ስርጭቱን ተደራሽ በማድረግ ለሀገር ግንባታ እያደረገ ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ክብርት ወይዘሮ ፋንቱ አሚኮ ከሀገር አቀፍ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጅ እና በክህሎት ተወዳዳሪ ሚዲያ ለመፍጠር እያደረገ ያለው ሥራ የሚደነቅ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ክልሉ ቴክኖሎጅውን በማዘመን በኩል የበኩሉን ድርሻ ይወጣልም ብለዋል። ሚዲያዉ አብሮነትን ሊያጠናክሩ የሚገቡ ሥራዎችን የበለጠ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
አሚኮ የአማራን ሕዝብ ባሕል፣ ልማትና እሴት በማስተዋወቅ በኩል የነበረውን ሚና ጠቅሰዉ ሚዲያውን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ክልሉ ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።
የውስጥ ገቢን በማመንጨት በተወሰነ የሰው ኀይል በአዲስ አበባ ስቱዲዮ ስርጭቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ የሚደነቅ መኾኑንም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።
በክልሉ ሕዝብ ላይ የሚነሱ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለመቀየር እና የክልሉን ታሪክ ፣ ባሕል እና ወግ ለማስተዋወቅ እየሠራ የሚገኘውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉኡሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!