በአማራ ክልል ከደን ልማት 1 ነጥብ 94 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

60

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደን ተከላ ሂደቱ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እንዲሁም ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ድርሻው ከፍተኛ እንዳለው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል።
ቢሮው ባለፈው ዓመት ከአጣና ሽያጭ፣ ከታክስ እና ከሮያሊቲ ከሚሠበሰበው ገቢ በተጨማሪ 1 ነጥብ 94 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጿል፡፡

ቢሮው በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የደን ልማት ውጤታማ መሆኑን አመላክቷል።

በ2014 ዓ.ም ክረምት ከተተከሉ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 79 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን ቢሮው አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምኅረት ከተተከሉ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 79 ነጥብ 7 በመቶ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡
የጽድቀት መጠኑ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች የተሻለ የጽድቀት መጠን ያላቸው ሲኾን፤ ቀሪዎቹ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ተከዜ ተፋሰስ አካባቢ፣ ደቡብ ወሎ በሽሎ ጎርጅ አካባቢ ዝቅተኛ የጽድቀት መጠን ያስመዘገቡ አካባቢዎች መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በስፋት ከጸደቁ ችግኞች መካከል በወል እና በግለሰብ ማሣዎች ላይ የተተከሉ ባሕር ዛፍ 83 በመቶ፣ግራቢሊያ 88 በመቶ፣ ዲከረንስ 85 በመቶ የተሻለ የጽድቀት መጠን እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ለችግኞች አለመጽደቅ ዋናው ችግር የመትከያ ጊዜያቸው መዘግየት እና የዝናብ ቀድሞ መውጣት በዋናነት ይጠቀሳሉ ነው ያሉት፡፡ የበልግ ዝናብ ቀድሞ የሚገባባቸው አካባቢዎች ለጽድቀት መጠኑ መጨመር አስተዋጽኦ እንደነበረውም አንስተዋል፡፡

በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች በአግባቡ መጽደቅ በ2005 ዓ.ም ዘጠኝ በመቶ የነበረውን የክልል የደን ሽፋን ወደ 15 ነጥብ 7 በመቶ አሳድጎታል፡፡ ይኽም ለምርታማነት መጨመር ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ ማንኛውም ሰው የተተከሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲጸድቁ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ አንድ ችግኝ ያጸደቀ ሰው የሚተነፍሰውን ኦክስጅን እንዳዘጋጀ ይቆጠራል ነው ያሉት፡፡
አቶ እስመለዓለም ችግኞች ሲተከሉ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለደን ልማት፣ ለመብራት እንጨት(ፖል) እና መሬትን ለማዳን በማለም ነው። ከጥቅም አንጻርመ ለማገዶ፣ ለኮንስትራክሽን እና ለአጣና ተብሎ የሚተከሉ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በዚህ ዓመት የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለመጨመር ለተከላ የደረሱ ችግኞችን ደረጃ ማውጣት፣ ዳስ ማንሳት፣ ሥር መገረዝ እና መሰል ተግባራት በግንቦት ወር በሥፋት የሚሠሩ ሥራዎች መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አርሶ አደሮችም ጉድጓዶችን ቀድሞ መቆፈር እና ለፀሐይ ማጋለጥ፣ የተተከሉትን መንከባከብ እና ልቅ ግጦሽን ማስቀረት እንደ ባሕል አድርገው እንዲወስዱት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሞሮኮ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ስምንት ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች ይሳተፋሉ።” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
Next articleአሚኮ የአማራን ሕዝብ ባሕል እና እሴት ከማስተዋወቅ ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጎልበት እየሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ክብርት ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋየ ተናገሩ።