የንጉሥ ተክለሃይማኖት ቤተ መንግሥትና በውስጡ ያሉ ቅርሶች ታሪክ መስካሪ መሆናቸው ቀርቶ ታሪክ እንዲሆኑ ስለምን ተፈረደባቸው?

297
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) ያደላቸው እና የቅርስን ምንነት የተረዱት ቻይናውያን በቤጂንግ እምብርት የሚገኘውን የነገሥታት መኖሪያ ‹‹የተከለከለው ከተማ›› በሚል ስያሜ በቱሪስት መዳረሻነቱ በስፋት አስተዋውቀውታል፤ በየቀኑም ሚሊዮኖች ይጎበኙታል። ይህ ቦታ የጥንታውያን ቻይና ከሚንግ እስከ ኪንግ ስርወ መንግሥት ድረስ የነበሩ ነገሥታት መኖሪያ ቦታ የነበረ ሲሆን የአሁኖቹ ቻይናውያን የአያት ቅድመ አያቶቻችን የታሪክ ማስረጃ ነው ብለው ጠብቀውታል። የቱሪስት መዳረሻ አድርገውትም በየዓመቱ ረብጣ ዶላር ያፍሱበታል።
 
ቻይናውያን የተከለከለው ከተማ የቱሪስት መዳረሻን ጨምሮ ሌሎቹን መንከባከብ በመቻላቸውን በየዓመቱ ከ59 ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝ ወደ ሀገራቸው ይገባሉ። ሀገሪቱ በቱሪስት ፍሰት ከፈረንሳይ፣ አሜሪካና ስፔን ቀጥላ በአራተኛነት ትገኛለች።
 
ሀገራችን ኢትዮጵያም የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ናት። እነዚህን ሀብቶች በሚገባ ለመጠበቅም ሆነ ለማስተዋወቅ የሚሠራው ሥራ ግን ከዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይ በአማራ ክልል የሚገኙ አብዛኞቹ ታሪካዊና የተፈጥሮ ቅርሶች አሁንም አደጋ ተጋርጦባቸዋል። እንደ ሀብት ሳይቆጠሩ እየፈራረሱ ይገኛሉ። ከእነዚህ በአደጋ ውስጥ ከሚገኙ የመስህብ ሀብቶች መካከልም በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የንጉሥ ተክለሃይማኖት ቤተ መንግሥት አንዱ ነው።
 
ቤተ መንግሥቱ በከተማዋ እምብርት ከመሬት ወለል በላይ 2ሺህ 446 ሜትር አማካኝ ከፍታ ላይ የሚገኝ ነው። የቤተ መንግሥቱ ውጫዊ ገፅታ እጅግ ማራኪና በትልልቅ ዛፎች የተከበበ ነው። እድሜ ጠገብ የኪነ ህንፃ አሻራነቱን ያረጋገጠ የግንብ አጥርም ዙሪያውን አካልሎታል። በውስጡም የነገሥታቱ መኖሪያ፣ ምግብ ማብሰያ፣ የግብር አዳራሽና ሌሎች ታሪካዊ ግንቦች ይገኙበታል።
 
ውስጣዊ የግቢውን ይዘት በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው የቤተ መንግሥቱ እምብርት ቦታ ነው። ይህ ክፍል 33 ሺህ ካሬ ሜትር የሚጠጋ ስፋት አለው። የነገሥታቱ መኖሪያ፣ ማብሰያ፣ የግብር አዳራሽ የሚገኙት በዚህ ቦታ ነው። በአንበሳ ቅርፅ የተሠሩ ወርቃማ ወንበሮች፣ የነገሥታቱና የመኳንንቱ መቀመጫ ወንበሮች፣ ቴሌፎንና ሌሎች መገልገያ ታሪካዊ ቁሶች ይገኙባቸውም ነበር።
 
በዚህ ወቅት እነዚህ የሀገር ሀብቶች በመውደም ላይ ናቸው። በነገሥታቱ መኖሪያ ውስጥ ይገኙ የነበሩ ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች በየቦታው ወደቀው ተመልክተናል። የማየት እድሉ ባይገጥመንም አብዛኞቹ ከጥንቃቄ ጉድለት እርጅና ተጫጭኗቸው እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎችም ነግረውናል። በማብሰያም ይሁን በግብር አዳራሹ ያሉ ህንፃዎችም ግድግዳቸው የፈረሰ፣ ኮርኒሳቸው የተቀዳደደና ወለላቸው ተቆፋፍሮ ገበጣ የመሰሉ ክፍሎች በግልጽ የበላቸው የበሮችና መስኮቶች ጣውላዎችም ይገኛሉ። ታሪክ መስካሪ መሆናቸው ቀርቶ ታሪክ እየሆኑም ነው። ዋናው ቤተ መንግሥት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የግለሰቦች መኖሪያ ሆኖ መቆየቱንም ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
 
አሁንም ግለሰቦች እየኖሩባቸው መሆኑን በታሪካዊ ቤቱ ውስጥ በምስላችን ያስቀረናቸው የመኝታ ፍራሽና ሌሎች መገልገያዎች ዋቢ ናቸው። ከዓመታት በፊት ይታወቁ የነበሩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ደብዛቸው እየጠፋ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል። በዙሪያው የሚገኙ ሌሎቹ የቤተ መንግሥቱ ክፍሎች ደግሞ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሆነው ይገኛሉ። በቤተ መንግሥቱ ምሥራቃዊ አቅጣጫ ባለው ክፍል የዞኑ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ህንፃ ሲገነባም ነባር ታሪካዊ ቤቶችን አፍርሶ መሆኑን ተዘዋውረን ተመልክተናል።
 
የደጃዝማች ፀሐይ እንቁሥላሴ መዝናኛ እንደነበር የሚነገርለት ታሪካዊ ቤትም ዛፍ ወድቆበት ተደርምሶም የድረሱልኝ ጩኸት እያሰማ ነው። ሌሎች የሰንደቅ ዓላማ መስቀያ፣ የመዝናኛና የመጋዘን ቦታዎች አሁንም በየቦታው ወድቀው በዙሪያው ‹ተፋረዱን› የሚሉ ይመስላሉ። ከጣውላ የተሰሩ የመስኮትና የበር ግንጣዮች ተሰባብረው በየቦታው ወዳድቀዋል።
 
ሁለተኛው የቤተ መንግሥቱ ክፍል ከእምብርት ቦታው እስከ ግቢው አጥር ድረስ ያካልላል። ይህ ቅጥር ግቢውን ከጠላት ለመጠበቅ ያገለግል የነበረ የደጀን ቦታ (ምሽግ) ነው። ከቤተ መንግሥቱና ከግብር አዳራሹ ጋር ተመሳሳይነት ባላቸው ሀገር በቀል ቁሳቁስ የተሠሩ ግንባታዎች ይታዩበታል።
ከውጭ በዋናው በር ወደ ውስጥ ሲገቡ በግንብ ከተሠራው አጥር ላይ በግራና ቀኝ የአንበሳ ቅርጾች አሉት። እሱን እንዳለፉ በቅጥር ግቢው በርከት ያሉ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ዙሪያውን ወርረውታል። ገቢዎች፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ … ሌሎቹም የመንግሥት ተቋማት ይገኙበታል። ከቤተ መንግሥቱ ጋር የማይገናኙ፣ የቤተ መንግሥቱን ታሪካዊነት የሚያደበዝዙ ቢሮ መሰል ቤቶች ተሰርተውበታል፤ የሳር መጋዝን የሚመስል የቆርቆሮ ቢሮም ጭምር ተሠርቷል።
 
የቤተ መንግሥቱ ወሰን በትክክል እንደማይታወቅና የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንደሌለውም አረጋግጠናል። አብመድ በጉዳዩ ዙሪያ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምርያ ኃላፊ ወይዘሮ ውዳለም አልማውን አነጋግሯል። ቤተ መንግሥቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጉዳት ሲደርስበትና ትኩረት ተነፍጎት የቆየ መሆኑን እርሳቸውም አስረድተዋል። አሁን ግን ልክ እንደ ሌሎች ጥንታዊ ቤተ መንግሥቶች እንክብካቤ እንደሚያስፈልገውና የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚችል የዞን አስተዳድሩ መረዳቱን ተናግረዋል። በቋሚነት በመኖሪያ ቤትነት ይጠቀሙት የነበሩ የዞኑ ባለሥልጣናትና የመንግሥት ተቋማት እንዲለቅቁ መደረጋቸውን ተናግረዋል። ‹‹አሁን ቤተ መንግሥቱን በቢሮነት እየተጠቀመ ያለው የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ነው። እስካሁን ያልወጣው ቤተ መንግሥቱን ይጠብቃል በሚል ስለነበር በቅርቡ ይወጣል›› ሲሉ ተናግረዋል። እርሳቸው የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ብቻ ነው ያለው የሚሉት ከቤተ መንግሥቱ እምብርት ላይ ያለውን ብቻ ወስደው ነው፤ ነገር ግን ቀደም ብለን የጠቀስናቸው ተቋማትም በቤተ መንግሥቱ ግቢ ውስጥ ናቸው፡፡
 
እንደ ወይዘሮ ውዳለም ገለፃ አካባቢው ከንክኪ ነፃ ከማድረግ ጎን ለጎን የጥገና ሂደቱን ለማስኬድ ታስቦ በበጀት እጥረት ምክንያት አልተሳካም። በበጀት ዓመቱ ቤተ መንግሥቱን ለማስጠገን የክልሉን መንግሥት ቢጠይቁም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አብራርተዋል። የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲኖረው ለማድረግም የቅየሳ ሥራው መጠናቀቁን፣ ካርታና ፕላኑ ደግሞ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
 
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ደግሞ ‹‹እድሳቱ የዘገየው ከእድሳቱ በፊት በምን ዓይነት መልኩ መጠገን እንደሚገባው ጥናት ስለሚያስፈልገው ነው›› ብለዋል። የሚያጠና ቡድን መቋቋሙን አስረድተዋል። ቤተ መንግሥቱ በከፋ ችግር ውስጥ መሆኑ እየታወቀ ለምን ቀድሞ የጥገና በጀት እንዳልተያዘ ተጠይቀውም ‹‹የቢሮው አቋም በዚህ ዓመት በጀት ተይዞ መጠገን ያለባቸው ከዓመታት በፊት የተጀመሩና በጥገና ሂደት ላይ ያሉት ብቻ ናቸው›› የሚል እንደሆነ አስረድተዋል። በያዝነው በጀት ዓመትም በክልሉ ከ18 በላይ ቅርሶች በ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎ ጥገና ላይ እንደሚገኙ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አረጋግጠዋል።
 
አብመድ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ቤተ መንግሥትን ቅርሶች አደጋ ላይ መውደቅና ለመስህብ ሀብትነት አለመዋል በተመለከተ ሲዘግብ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ በሬዲዮ፣ በጋዜጣና በማኅበራዊ ገጾቹ ለዓመታት እየዘገበ፤ ተመሳሳይ ችግሮችንም እያመለከተ ነው፤ የተግባር ምላሾች ግን በዓመታት ሂደት ውስጥም ጎልተው አልታዩም፡፡
 
ዘጋቢ:- ሀይሉ ማሞ
Previous articleየደባርቅ ጃናሞራ-በየዳ መንገድ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ተዘግቶ መንገደኞች እየተጉላሉ መሆኑን ገለጹ፡፡
Next articleወጣቱም በስሜትና አሉባልታ እየተነዳ ጥፋት ከመሥራት መቆጠብ እንዳለበት የአማራ እና ኦሮሚያ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ተናገሩ፡፡