“የአማራ ክልል ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ ሰላማዊ የትግል ስልትን መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው’’ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)

114

እንጅባራ፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን በሚል መሪ ሃሳብ’’ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ኮንፈረንስ በእንጅባራ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በወቅታዊ ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ በሚመክረው በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ኮንፈረንሱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ድሎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመገምገም የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በሰላማዊ የትግል አማራጭ ብቻ ነው ያሉት ዶክተር ዘሪሁን ከዚህ ውጭ የኾኑ አካሄዶች ለክልሉ ሕዝብም ለሀገርም የማይበጁ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ እየተስተዋለ ያለው አውዳሚ የትግል ስልት የክልሉን ሕዝብ ለከፋ ችግር እየዳረገ በመኾኑ እንዲህ አይነት የጽንፈኝነት አስተሳሰቦችንና ተግባራትን መታገል ከሁሉም የሚጠበቅ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው በበኩላቸው ኮንፈረንሱ በአመራሩ መካከል የአመለካከትና የተግባር አንድነት በማምጣት የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ አቋም የሚያዝበት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ አመራሩ በክልሉ የተጋረጡ ስጋቶችን በጥልቀት በመረዳት የመፍትሔው አካል እንዲኾንና ለተግባራዊነቱም ቁርጠኝነቱን የሚያረጋግጥበት እንደሚኾን የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ዓለማየሁ ገበየሁ ናቸው፡፡

በኮንፈረንሱ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ከ5 መቶ በላይ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረሱ ችግሮችን ለመቀልበስና የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
Next articleታሪክ ሕያው ምስክር ነው!