በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረሱ ችግሮችን ለመቀልበስና የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

77

ደብረ ማርቆስ፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞንና ደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ለ3 ቀናት የሚቆይ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ማካሄድ ጀምረዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞንና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች “ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ሕዝባችንን እናስከብራለን” በሚል መሪ ቃል በደብረ ማርቆስ ከተማ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ማካሄድ ጀምረዋል፡፡

በቅርቡ በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡትን የአማራ ክልልና ብልፅግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል የነበሩትን አቶ ግርማ የሽጥላን በማሰብ የተጀመረው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ፤ በአማራ ሕዝብ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን እና የሕዝቡን የልማትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በተደራጀ መልኩ እንዲፈቱ የሚያስችል ውስጣዊ አንድነትን ለመፍጠር ያለመ ኮንፈረንስ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ኃላፊ አቶ አብተው መኳንንት ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ኀላፊ አቶ ዋለ አባተ የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በርካታና መዋቅራዊ በመኾናቸውና ችግሮችን ለመፍታት የሌሎችን የኀብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የሚጠይቅ በመኾኑ መላው ሕዝብና አባላቱ የጥያቄዎችን ይዘትና በምን መልኩ መፍታት እንደሚገባ በውል መገንዘብ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ፓርቲው የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ለመፍታት እየሠራ ቢኾንም በውስጣዊ አንድነት ችግር እና በውጫዊ የፖለቲካ አሻጥር ምክንያት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ በአማራ ክልል ብቻ የሚካሄድ መኾኑን የገለጹት አቶ ዋለ ከውስጣዊ ችግሮች ባለፈ ውጫዊ የፖለቲካ አሻጥሮችን ለመቀልበስ የአመለካከት ብዥታዎችን ማጥራት፣ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከርና የጋራ ጥያቄዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ መታገል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አቶ ቢያዝን እንኳሆነ፤ የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄች ለመፍታት ክልላዊና ሀገራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ውጫዊ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችሉ ሃሳቦችና ስልቶችን በማፍለቅ የሕዝቡን መሰረታዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ውይይት ማካሄድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ ለ3 ቀናት የሚቆይ ሲኾን ከዞኑና ከከተማ አሥተዳደሩ የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፦ንጉስ ድረስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የውስጥ አንድነትን በማጠናከርና በመደማመጥ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መታገል ይገባል” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደሪ ወርቁ ኃይለማሪያም
Next article“የአማራ ክልል ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ ሰላማዊ የትግል ስልትን መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው’’ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)