
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) መንገደኞች ለአብመድ በስልክ እንዳስታወቁት ትናንት ከበየዳ ወደ ደባርቅ ይጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከቀኑ 5፡40 ላይ ደባርቅ ወረዳ ሳንቃበር አካባቢ ከሚገኝ አደገኛ ቁልቁለት ላይ ወደኋላ ተንሸራትቶ መንገድ ላይ ወድቋል፡፡ መንገዱ በከፊል እንደተዘጋ ከደባርቅ በኩል ጠጠር ጭኖ ወደ በየዳ ይሄድ የነበረ ገልባጭ የጭነት መኪና ደግሞ ከቀኑ 9፡00 አካባቢ ተጠግቶ ለማለፍ ባደረገው ሙከራ ማለፍ ሳይችል ከወደቀው መኪና ላይ ተደግፎ ቆሟል፤ በዚህም መንገዱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል፡፡
መንገደኞቹ እንዳሉት ወደ ደባርቅ በመደወል የሚመለከታቸውን የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ተቆጣጣሪዎች ወደ ቦታው ሄደው መፍትሔ እንዲሰጡ ቢጠይቁም ይህ ዜና አየር ላይ እስከዋለበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኙም፡፡ በዚህም ከደባርቅ ወደ በየዳና ጃናሞራ እንዲሁም ከበየዳና ጃናሞራ ወደ ደባርቅ የሚደረግ የተሽከርካሪ ጉዞ ሙሉ በሙሉ መቆሙን ተናግረዋል፡፡
‹‹ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚሄዱ እና ከፓርኩ የሚመለሱ ጎብኝዎች እና ከየወረዳዎቹ ለሥራና ሕክምና የሚንቀሳቀሱ መንገደኞች ለችግር ተዳርገዋል›› ብለዋል መንገደኞቹ ለአብመድ ሲናገሩ፡፡
በአሽከርካሪው ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ በአደጋው በሁለት ሰዎች ላይ ብቻ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የገለጹት መንገደኞቹ ‹‹ከመንገዱ አደገኛነትና ከመልክአ ምድሩ አስቸጋሪነት የተነሳ አደጋው የከፋ ይሆን ነበር፤ ነገር ግን በከባድ ዳገት ምክንያት መኪናው ሲንሸራተት ሾፌሩ መሪ ጠምዝዞ መኪናውን ወደ ገደል እንዳይገባ በማድረግ ብዙዎቻችንን ታድጎናል›› ብለዋል፡፡
የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው ጭነት ልኩ በላይ ሰዎችን ይዞ እንደነበር ያመለከቱት መንገደኞቹ ምን ያህል እንደሆኑ በእርግጠኝነት መናገር አልቻሉም፡፡
የደባርቅ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክር ቢሆነኝ እልፍአስግድ በስልክ ለአብመድ በሰጡት መረጃ ‹‹ትናንት ከሰዓት በኋላ አንድ አውቶቡስ መውደቁን ሰምተናል፤ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎችም በአጋጣሚ በዚያው የነበረ አምቡላንስ ወደ ሕክምና አድርሷል፤ የወደቀው መኪና ግን መንገድ አልዘጋም ነበር›› ብለዋል፡፡ ትናንት ዝናብ ስለነበርና የጽሕፈት ቤቱ መኪናም በሌላ ስምሪት ስለነበር ባለሙያ ወደ ቦታው እንዳተላከ የገለጹት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ዛሬ ረፋድ 3፡40 ላይ ለአብመድ ሲናገሩ ‹‹ከአስር ደቂቃ በፊት ነው መንገድ መዘጋቱ የተነገረኝ፤ አሁን ባለሙያዎች ሊሄዱ ነው፤ ሁኔታውን ተመልክተው እንዳሳወቁን ቀጣዩን መፍትሔ እንወስናለን›› ብለዋል፡፡
መንገዱ የተበላሸና ተደጋጋሚ አደጋ የሚደርስበት መሆኑን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ቢሆነኝ ‹‹መንገዱ እንዲጠገን በየጊዜው ብንጠይቅም ምላሽ የለም፤ የደባርቅ -ሳንቃበር-ቧኂት ብቻ ሳይሆን የደባርቅ -ሊማሊሞ-ዛሪማ መንገድም በተደጋጋሚ ብልሽት ለአደጋ ተጋለጧል፤ ቀድሞ መንገዶችን የሚጠግን ግን የለም›› ብለዋል፡፡
በአደጋው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ መረጃ እንደሌላቸውና የጉዳት መጠኑ ግን ቀላል እንደሆነ መስማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የደባርቅ- ጃናሞራ-በየዳ መንገድ ከደባርቅ በበለስ-መካነ ብርሃን- ቧኋት ከስሜን ተራራዎች ፓርክ ውጭ እየተገነባ በመሆኑ የደባርቅ-ሳንቃበር-ቧኂት መንገድ በቂ ጥገና እያገኘ አይደለም፤ በዚህም ለብልሽት ተዳርጓል፡፡ አዲስ በግንባታ ላይ የሚገኘው መንገድ ደግሞ ከአምስት ዓመታት በላይ ተጓትቶ በከፊል ከተቋራጩ ተነጥቆ ለመከላከያ ኮንስትራክሽን ከዓመታት በፊት ተሰጥቷል፤ ነገር ግን መንገዱ አሁንም ባለመጠናቀቁ አስቸጋሪ በሆነው የፓርኩ ውስጥ መንገድ ኅብረተሰቡ እየተቸገረ መሆኑን ወረዳዎቹ በየጊዜው ቅሬታ ያቀርባሉ፤ አብመድ ተደጋጋሚ ዘገባዎችን ሠርቷል፤ የተግባር ምላሽ ግን አልተሰጠም፡፡
ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት
ፎቶ፡- ሀውልቱ ሙሉጌታ