
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ600 በላይ የዞንና የወረዳ መሪዎች የተሳተፉበት ድርጅታዊ ጉባኤ እየተካሔደ ነው።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማሪያም ለውጡን በተገቢው መንገድ ለመምራት ቀዳሚው የውስጥ አንድነት ማረጋገጥና ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የውስጥ አንድነቱ የጠነከረ ሕዝብ ይደመጣል፣ ይከበራል ኃይሉንም ያሰባስባል ያሉት አቶ ወርቁ የአማራ ሕዝብ ከቦታ ቦታ በነፃነት ተዘዋውሮ የመሥራት ፣ የእኩልነትና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መሥራት ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ ጣዕምያለው ለውጡ ተስፋና ስጋትን ይዞ መምጣቱን አመላክተው የአማራ ሕዝብ በማንነቱ መሳደድ፣ ግድያ፣ መፈናቀልና የሚገለልበት ኹኔታ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ማስተካከልን የሚጠይቅ እንደኾነ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።
በተበተነና በተዳከመ መዋቅር ሕዝብን ማሻገር አይቻልም ያሉት አቶ ብርሃኑ የአማራ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ መሰባሰብና በሥርዓት መራመድን ይጠይቃል ነው ያሉት።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው ጉባኤው ጥንካሬዎችን ለማጎልበትና ድክመቶችን ለማረም አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
“ፈተናን ወደ ድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሔደ የሚገኘው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመሪዎች ድርጅታዊ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!