
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓባይ ተፋሰስ ላይ ለሚሠሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች የፌደራል መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባ ተጠይቋል፡፡
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊት ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ብቻ በዓመት 140 ሚሊዮን ቶን አፈር ተሸርሽሮ ከሀገር ይወጣል፡፡ 60 በመቶ የሚኾነው ወደ አስዋን ግድብ የሚገባው ደግሞ ከኢትዮጵያ ተሸርሽሮ የሄደ አፈር ነው፡፡
በጥናቱ እንደተገለጸው ባለፉት 40 ዓመታት የአባይ ተፋሰስ የአፈር መሸርሸር መጠን በ15 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ በ1960ዎቹ ከ1 ሊትር የዓባይ ውሃ ሲገኝ የነበረው 3 ግራም አፈር ሱዳን ጠረፍ አካባቢ ወደ 5 ግራም ማደጉን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የግድቡን መፃኢ ችግሮች ለመፍታት በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በአባይ ተፋሰስ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ መሥራት እንዳለበት ማንሳቱ ይታወቃል፡፡
የዓባይን ግድብ ከደለል ለመከላከል በክልሉ በኩል እየተሠራ ያለውን ሥራ በተመለከተ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አልማዝ ግዜው እንዳሉት የአማራ ክልል የዓባይ መነሻ እና የበርካታ ውኃማ አካላት መገኛ ነው፡፡ የክልሉን ተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅና በክልሉ የሚገኙ ውኃማ አካላትን ከደለል ለመከላከል ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መሠራቱን ነግረውናል፡፡ በተሠራው ሥራም የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት በክልሉ ከነበረው 14 ነጥብ 5 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 15 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በመጪው ክረምት በክልሉ በ200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ በተፋሰሱ የማልማት ሥራ እንደሚራ ገልጸዋል፡፡
ኀላፊዋ እንዳሉት በአባይ ተፋሰስ ላይ በሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች የፌደራሉ መንግሥት ሚና ዝቅተኛ ነው፡፡ የአማራ ክልል በብዛት የዓባይ ተፋሰስ መነሻና እና ከፍተኛ ቦታ የሚበዛበበት በመኾኑ ግድቡን ከደለል ለመከላከል ክልሉ ከሚያደርገው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ባለፈ የክልሎችና የፌደራል መንግሥት ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚጠይቅ አንስተዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የፌደራል መንግሥት በበጀት ጭምር መደገፍ እንሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
ዘጋቢ፦ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
