
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የባሕር ዳር ከነማ የቦርድ ሠብሳቢ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በዛሬው እለት በክለቡ ደጋፊዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘዋል።
“ክለባችን ባሕር ዳር ከነማ በዘንድሮው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ዋንጫ ለማንሳት እየተፎካከረ ይገኛል” ያሉት ከንቲባ፤ ይህንን መሠረት በማድረግ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ከኾነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር ለሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ የክለባችን ደጋፊዎች በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው በአካል ተገኝተው ለመደገፍ ጉዞ ወደ ሀዋሳ ለማድረግ ዝግጅት ጨርሠው ወደ ተዘጋጀላቸው አውቶብስ እየገቡ ባሉበት ሁኔታ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት በተወረወረ ቦንብ 23 የክለባችን ደጋፊወች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት በመድረሡ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በከተማችን ላይ እየተፈፀመ ያለው የቦንብ ጥቃትና ግድያ የከተማችንን ነዋሪ በሠላም ወጥቶና ተንቀሳቅሶ የመሥራት ፍላጎት የሚገድብ፣ የከተማችንን እድገትና ልማት የሚጎዳ፣ ብሎም የከተማችንን ገፅታ የሚያበላሽ የፀረ ሰላም እንቅስቃሴ በመኾኑ መላ ኅብረተሰባችን ሊያወግዘው ይገባል። ከዚህ ባለፈ ኅብረተሰቡ የጸጥታው ባለቤት በመሆን ከጸጥታ ኃይላችን ጎን በመሠለፍ የከተማችንን ሰላም የሚያውኩ አካላትን በመለየት ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ ይገባል።
የከተማችንን የፀጥታ አካላት ደከመኝ ሠለቸኝ ሳይሉ የከተማችንን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየሠሩ ይገኛሉ ያሉት ዶክተር ድረስ፤ አኹንም እንደከዚህ ቀደሙ እነዚህን ወንጀል ፈፃሚወች ተከታትለው ለህግ የሚያቀርቡ ይኾናል ብለዋል። ለዚህ ተግባር መሳካት የመላ ሕዝቡ ትብብር አስፈላጊ በመኾኑ ለከተማችን ሰላም መረጋገጥ ኹላችንም እንድንረባረብ ጥሪ አቀርባለሁ በሚል ዶክተር ድረስ መልእክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
