
ሰቆጣ ፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ሁኔታዎችና የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙርያ ከዞንና ከወረዳ አመራሮች ጋር ውይይት ማካሄድ ጀምሯል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ የዛሬው ውይይት የክልላችንና የዞናችንን የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመገመገመ ያለመ ነው ብለዋል።
አቶ ዳግም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በክልላችንና በዞናችን እያጋጠመ ያለውን ችግር በድል ለመሻገር ፅንፈኝነት የሕዝቡና የፓርቲው አደጋ በመኾኑ በቁርጠኝነት የምንታገለው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) በውስጣችን ያሉ የአመራር አንድነት ጉድለቶችን በማረም የሕዝባችን አንገብጋቢ ችግሮች በኮንፈረንሱ ላይ ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።
አሥተዳዳሪው በዞናችን ቃል ተገብተው ያልተጀመሩና ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ በርካታ መሰረተ ልማቶች የሚገኙ በመኾኑ እነዚህን በመለየት በቀጣይ እንዲሰሩ ግፊት ይደረጋልም ብለዋል።
ዶክተሩ በሕዝባችን የሚነሱ የማንነትና የወሰን ጉዳዮችም እልባት እንዲያገኙ በኮንፈረንሱ ይመከራል ነው ያሉት።
ወይይቱ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚካሄድ መኾኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሰሎሞን ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
